የሃይማኖት አባቶች መሰረቱን በሰላም ላይ የሚጥል ትውልድ ማፍራት ይገባል አሉ

ታኅሣሥ 23/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያን አንድነትና ቀጣይነት ለማረጋገጥ በእውቀት የታነፀ እና መሰረቱን በሰላም ላይ የሚጥል ትውልድ ማፍራት እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ፡፡

በአሸባሪው ትሕነግ የወደመውን የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የጎበኙት የሃይማኖት አባቶቹ ውድመቱን ‘ኢትዮጵያዊ ስነ ልቦና ያለው አካል አደረገው ለማለት አያስደፍርም’ ብለዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን ከኢትዮጵያዊነት ስነ ምግባር ያፈነገጠ፣ የትውልዱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የማያሳስበው አረመኔ መሆኑን ያሳየበት ነው ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

የሃይማኖት አባቶቹ የወደሙ ተቋማትን ከቀድሞው በተሻለ መልኩ መገንባት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት በመሆኑ በአንድነት መቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ወገኑን የሚያከብርና አገሩን እንደ ጥንት አባቶች የሚወድ ትውልድ ለማፍራት የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ሁሉም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡