የህወሓት የጥፋት ቡድን ላይመለስ ተደምስሷል- ዶ/ር ቀነዓ ያደታ

                                    የመከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር ቀነዓ ያደታ

የህወሓት የጥፋት ቡድን ላይመለስ ተደምስሷል ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር ቀነዓ ያደታ ገለጹ።

የመከላከያ ሚኒስትሩ በህወሓት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው በህግ ማስከበርና ህልውና ዘመቻው ወቅት ዕጅ ሰጥተው በደቡብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል የተሃድሶ ስልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙትን የትግራይ ክልል  ልዩ ሃይል እና የሚሊሻ አባላትን  ባወያዩበት ወቅት ነው ይህን ያሉት።

የመከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር ቀነዓ ያደታ በዚህ ወቅት ”ደም መጣጩ ቡድን እናንተን እሳት ውስጥ ማግዶ ተደምስሷል” ብለዋል፡፡

ትህነግ ለግል ጥቅሙ እና ለስልጣን ጥማቱ ሲል እኩይ ተግባራትን በኢትዮጵያውያን ላይ ፈጽሞ ላይመለስ ተወግዷል ሲሉም አክለዋል፡፡

”እናንተ ግን በውሸት ወሬ ሳትረበሹ ስልጠናችሁን በማጠናቀቅ ወደ ሰላማዊ ህይወታችሁ መመለስ አለባችሁ” ብለዋል፡፡

የህብረት ስልጠና ዋና መምሪያ ሀላፊ ሌ/ጀ ሀሰን ኢብራሂም በበኩላቸው፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከጁንታው ጋር የተሰለፉ ዜጎችን ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

እጅ የሰጡት አባላት በበኩላቸው”ግዴታ ሆኖብን ብንሰለፍም ምንም ሳንተኩስ እጃችንን ከሰጠንበት ጊዜ አንስቶ የመከላከያ ሰራዊታችን እያደረገ ላለው እንክብካቤ ምስጋና እናቀርባለን” ብለዋል፡፡ በቀጣይ ለሃገራቸው ሰላም በጋራ እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል፡፡

እጅ ሰጥተው በደቡብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል የተሃድሶ ስልጠና በመውሰድ ላይ ከሚገኙት 764 ዜጎች ጋር በተደረገው ውይይት ላይ የመከላከያ ሚኒስትሩ እና ሌ/ጀ ሀሰን ኢብራሂምን ጨምሮ ሌሎች ጀነራል መኮንኖች እና የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ነቢዩ ስሁል መገኘታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ የትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡