የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪካ ህብረት ብቻ እንዲከናወን የቀጣዩን የአፍርካ ህብረት ሊቀመምበርነት ቦታን ከደቡብ አፍሪካ ለምትረከበው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኩል ገለጻ መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢትዮ- ሱድን የድንበር ጉዳይን በተመለከተም ከሰሞኑ በተዘጋጀ የዲፕሎማቶች አውደ ጥናት ላይ እንደተመከረበት የሚኒስቴሩ ቃልአቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ አብራርተዋል፡፡
ሱዳን እያደረሰች ያለውን ትንኮሳም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ተጠናክሮ መቀጠሉን እና ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ጉዳይ ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ የማስረዳት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የውጭ አምባሳደር ዲና አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሀገሪቱ ፖለቲካል ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ በገፅ ለገፅና ዌብነር መድረኮች ከተለያዩ ዲፕሎማቶች ጋር ውይይት እንዳደረጉም ተገልጿል፡፡
ሀገሪቱ እያከናወነች ባለው የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ባሳለፍነው ሳምንት 916 ስደተኞችን ወደ ሀገር ቤት ማስገባት እንደተቻለም ተጠቅሷል፡፡
(በደምሰው በነበሩ)