የሆቴል ቱሪዝም ኢንቨስትመንትን በማጠናከር የክልሉን እምቅ ሀብት ለመጠቀም ይሰራል

ሚያዝያ 22/2014 (ዋልታ) የሆቴል ቱሪዝም ኢንቨስትመንትን በማጠናከር የክልሉን እምቅ ሀብት ለመጠቀም እንደሚሰራ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ገለፀ።
ወደ 1 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ የተደረገበት ታላቁ ሳላይሽ ሆቴልና ስፓ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ከመምህርነት ሙያ ጀምሮ ስኬታማ የንግድ ሰው የሆኑት ባለሃብቱ አብርሃም አዘረፈኝ እና ባለቤታቸው ምንዳየው ስጦታው በአብሮነት አንሳ ከማትታየው ሳላይሽ እስከ ታላቁ ሳላይሽ ዘልቆ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብቸኛውን ባላ አራት ኮከብ ሆቴልና ስፓ እስከ መገንበት ደርሷል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ ፀጋዬ ማሞ ክልሉ ሠፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሉት በመሆኑ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ ቢመጡ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ትብብር ያደርጋል ብለዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የሆቴል ቱሪዝሙ ዘርፍ በመዘመን የቱሪስቶችን ፍሰት በመጨመር በክልሉ የሚከናወኑ የኮንፈረንስ ቱሪዝምን በማገዝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ሆቴልና ስፓ ለምርቃት በቅቶ በማየት መደሰታቸውን ገልፀዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቀበሌ መንገሻ ኢንቨስትመንቶች የሥራ ዕድልን በመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስረፅ እንደ ሀገር ከፍተኛ ሚና ስላላቸው ባለሀብቶች በዞኑ መጥተው ቢያለሙ ውጤታማ ይሆናሉ ብለዋል።
በምርቃቱ ላይ የተገኙት የጋምቤላ ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ ላክዴር ላክባክ ከለውጡ በፊት የነበሩ ኢንቨስተሮች መሬትን ያለ አግባብ በመወሰድ የሀገር ሀብት ማባከናቸውን ገልጸው ዛሬ በሚዛን ቴፒ ከተማ የተመረቀው ሆቴል የከተማ ኢንቨስትመንትን የሚያነቃቃ ነው ብለዋል።
በቤንች ብሔረሰብ ዘንድ የሚሰጠው ትልቁ የባህል ማዕረግ ኮምት ለባለሃብቱ አብርሃም አዘረፈኝ የተሰጠ ሲሆን ባለቤታቸው ደግሞ ምንዳየው ስጦታው ደግሞ ኮምኒን ተብለው ተሰይማዋል።
አክሊሉ ሲራጅ (ሚዛን አማን)