የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ኢትዮጵያን ለእድገት የምታደርገውን ትግል የሚያግዝ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

ሚያዚያ 21/2014 (ዋልታ) የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ኢትዮጵያን የሚመጥን፣ ለእድገት የምታደርገውን ትግል የሚያግዝ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀን 10 ሺህ ቶን ሲሚንቶ እንዲያመርት እቅድ ተይዞለት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ለሚ ከተማ እየተገነባ ያለውን የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የግንባታ ሂደትን ጎብኝተውታል።

የለሚ ሲሚንቶ ፕሮጀክት ከምንፈልጋት የወደፊቷ ኢትዮጵያ ጋር ድልድይ ሆነው ከሚያገናኙን በርካታ ታሪካዊ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ሰሜን ሸዋ ትልቅ የመልማት ዐቅም ያለው አካባቢ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ፍላጎት ጋር የሚጣጣሙት እንዲህ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ይህንን ዕምቅ ዐቅም ለመጠቀም ያግዛሉ ሲሉም አክለዋል።

በመጠነ ሰፊ ዕይታ መርሖዎች ላይ ተመሥርተው ሙዓለ ንዋይ የሚያፈስሱ፣ ጥራት እና ፈጣን አቅርቦት ላይ አተኩረው የሚሠሩ ባለሀብቶች የእኛ ዋነኛ አጋሮች ናቸውም ብለዋል።

ኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ ኩባንያ ከቻይና ባለሀብቶች ጋር በመሆን እየገነቡት ያለው ፋብሪካው፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲገነቡ እቅድ ከተያዘላቸው ስድስት ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ እንደሆነ በጉብኝቱ ወቅት ተጠቅሷል።

ኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ ከቻይና ባለ ሀብቶች ጋር በመሆን የያዛቸው ስድስቱ ፕሮጀክቶች፡-

  1. በቀን 10ሺህ ቶን ሲሚቶ የሚያመርት ፋብሪካ
  2. 30 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ጂብሰም ቦርድ እና 400 ሺህ ቶን የዱቄት ጂብሰም በአመት የሚያመርት ፋብሪካ
  3. በድሬዳዋ በቀን 3 ሺህ 500 ቶን ሲሚንቶ ለኤክስፖርት የሚያመርት ፋብሪካ
  4. የድሬዳዋውን ነባር ፋብሪካ 30% የሚያሳድግ ፕሮጀክት
  5. በአመት 350 ሺህ ቶን ብረት ማምረት የሚችል ፋብሪካ (በጥናት ላይ የሚገኝ)
  6. ዳውሮ የድንጋይ ከሰል ማእድን ማውጫና ማጠብያ ናቸው

ለፕሮጀክቶቹ የሁለት ዓመት የግንባታ ጊዜ በእቅድ የተቀመጠላቸው ሲሆን ለመጀመርያ ዙር 600 ሚሊየን ዶላር በጀት ተይዞላቸዋል።

ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በመሉ የ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንቶች እንደሆኑ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፋብሪካው ኢትዮጵያን የሚመጥን፣ ለእድገት የምታደርገውን ትግል የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ በጥራትና በፍጥነት መጠናቀቅ አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስትም ለፕሮጀክቶቹ አጋር ሆኖ ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውን የኢብኮ ዘገባ ጠቁሟል።

በጉብኝቱ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የማእድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና ሌሎችም ተገኝተዋል።