የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚያጠናከር ውይይት እያካሄደ ነው

ሚያዚያ 13/2014 (ዋልታ) የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ያለውን የኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ለማጠናከር በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛል::

በኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ እና እውቀታቸውንና ሀብታቸውን ፈሰስ በማድረግ ላይ የሚገኙ ባለሀብቶች እንደ ሀገር የተጀመረውን እድገት እና ልማት ከማሳለጥ አኳያ አይተኬ ሚና እንዳላቸው የከተማዋ ከንቲባ በሪሶ ተመስገን ገልፀዋል፡፡

በከተማዋ ከ50 በላይ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመሰማራት በርካታ ቁጥር ላላቸው ነዋሪዎች የስራ እድል መፍጠራቸው ተገልጿል::

የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት የከተማዋ የኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ጽ/ቤት ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ባለሀብቶች ፍቃድ መስጠቱም ተገልጿል::

ባለሀብቶች ያላቸውን እውቀትና አቅም በማሰባሰብ ኢትዮጵያ ካላት የተፈጥሮ ፀጋዎች ጋር በማወዳጀት ሀገርን የማልማትና እድገቷን የማረጋገጥ ትልቅ ሀላፊነት እንዳለባቸው በመገንዘብ ሊሰሩ ይገባል ተብሏል::

በሔብሮን ዋልታው