በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ የተሰራው አዲሱ የላፍቶ አትክልት እና ፍራፍሬ መገበያያ ማዕከል የግብይት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል ።
አዲሱ የላፍቶ አትክልት እና ፍራፍሬ የመገበያያ ስፍራው የግንባታ ሂደት የመጀመሪያው ምዕራፍ 99 በመቶ የመገበያያ ሼዶች በመጠናቀቃቸው ከጃንሜዳ የተነሱ ነጋዴዎች በከፊል የንግድ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ።
በስፍራው የአትክልት እና ፍራፍሬ ግብይት በጥሩ ሁኔታ በመከናወን ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ ገልጸዋል ።
የመጀመሪያ ቀን እንደመሆኑ ከፈቃድ እና የቲን ቁጥር ጋር በተያያዘ የአየር በአየር ሽያጭ የተስተዋለ ሲሆን ከነገ ጀምሮ የግብይት ስርዓት የማስያዝ ስራ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አቶ አብዱልፈታ ገልጸዋል፡፡
ማዕከሉ የመንገድ ፣የመብራት፣የመጸዳጃ ቤት እና አስፈላጊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች የተሟሉለት ሲሆን በ80 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ14 ሼዶች 588 የመገበያያ ሱቆችን አካቷል ፡፡
(ምንጭ፡-የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት)