የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች ለህልውና ዘመቻው ከ36 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ወሰኑ

ነሃሴ 13/2013 (ዋልታ) –የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ሰራተኞች ለህልውና ዘመቻው ከ36 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ወሰኑ።

የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሰራተኞች ዛሬ ባካሄዱት ውይይት የአንድ ወር ደመወዛቸውን በመስጠት ከ36 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ወስነዋል።

አመራሮቹና ሰራተኞቹ ውይይታቸውን ሲያጠናቅቁ ለመከላከያ ሰራዊት ደም በመለገስ አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል።

የሀገርን ህልውና ለማስከበር በግንባር እየተፋለሙ ላሉ የሰራዊት ቤተሰቦች አባላት ነፃ የትምህርት ዕድል ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሰራተኞች ዛሬ ባደረጉት ውይይት  ከገንዘብ ድጋፉ በተጓዳኝ ስራቸውንና ሀላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ለሀገር ያላቸውን ክብር በተግባር ለማረጋገጥ ቃል ገብተዋል።

የተደረገው ድጋፍ ሰራዊቱ  የሀገርን ሰላምና ህልውና ለማስጠበቅ እየከፈለ ካለው መስዋእትነት አንጻር አነስተኛ በመሆኑ ወደፊትም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ህወሃት በከፈተው ጦርነት ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ወገኖች  ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ቁሳቁሶችንና ምግቦችን በድጋፍ ማበርከቱን  የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጄይላን ወሊዪ ለኢዜአ ገልጸው ነበር።