የሕወሓት ቡድን  በሰሜን ወሎ ዞን 832 ትምህርት ቤቶች ከጥቅም ውጭ ማድረጉ ተገለጸ

ጥቅምት 18/2014 (ዋልታ) አሸባሪው እና ወራሪው የሕወሓት ቡድን ለወራት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በፈጸመው ወረራ እና ምዝበራ በሰሜን ወሎ ዞን ብቻ 832 ትምህርት ቤቶች ከጥቅም ውጭ ማድረጉን የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።
የሽብር ቡድኑ በዞኑ በፈጠረው ዘርፈ ብዙ ችግር በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ከ330 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ለመሆን ተገደዋል ሲሉ የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰጠ ታደሰ ተናግረዋል።
የትምህርት ሥራ በባህሪው በእቅድ እና ቅደም ተከተል የሚመራ ነው ያሉት ምክትል መምሪያ ኃላፊው ሁሉም ትምህርት ቤቶች ሃብትና ንብረታቸው በመዘረፉ እና ሽብርተኛው የጦር ካምፕ አድርጓቸው ስለነበር መማር ማስተማሩን በቅርብ ለመጀመር ፈታኝ ይሆናል ብለዋል።
ማኅበረሰቡ በጭንቅ ውስጥም ሆኖ ያረሰውን የተወሰነ ሰብል የሽብርተኛው ወራሪ ቡድን አባላት ሰለጨፈጨፉበት እና ስለዘረፉበት በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል ከ265 ሺህ በላይ የሚሆኑት የትምህርት ቤት ምገባ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።
የሽብርተኛው ወራሪ ቡድንን በተባበረ ክንድ በመደምሰስ አካባቢውን በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረግ ጊዜ የሚሰጠው አለመሆኑን ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰጠ መግለፃቸውን አሚኮ ዘግቧል።