የሕዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ 45 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል – አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)

ሰኔ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 45 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ም/ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ገለጹ።

“የመገናኛ ብዙኃን ሚና ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ” በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር ፎረም እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ም/ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም የመገናኛ ብዙኃን የሕዳሴ ግድቡ 96 በመቶ እንዲደርስ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ አመስግነዋል።

ሆኖም ግን 96 በመቶ ግንባታው የተጠናቀቀውን ሕዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ ሁሉም ሚዲያዎች መረባብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በተለይም የግድቡን ታሪክ፣ አመሰራረት እና ጅማሮ እንዲሁም የግንባታ ሂደት ለዓለም በማሳወቅ እና በመሰነድ በኩል ለመጭው ትውልድ ማሻገር እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የዓለምን ኢኮኖሚ የተቆጣጠሩ ሀገራት በርዳታና ድጋፍ ሰበብ በራሳችን ሰርተን እንዳንለወጥ እጅ እና እግርን የሚያስሩ እንጅ የእውነት የሚደግፉ አለመሆናቸውን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ተረድተን እንደጀመርነው ግድቡን በመረባረብ ማጠናቀቅ አለብን ሲሉም ገልጸዋል።

በአመለወርቅ መኳንንት