የሕዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር በሙኒክ ተካሄደ


ሐምሌ 19/2013 (ዋልታ) –
“ደግሞ ለዓባይ” በሚል ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ መርኃግብር በጀርመን ሙኒክ ተካሄደ።
በፕሮግራሙ ላይ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቦንድ ግዥ፣ በመጽሔት ሽያጭና በስጦታ “ደግሞ ለዓባይ” በማለት በከፍተኛ ቁጭትና ፍላጎት የተሳተፉ ሲሆን፣ በዚህም ከ15 ሺህ ዩሮ በላይ ገቢ ማሰባሰብ ተችሏል።
በጀርመን ፍራንክፈርት የኢፌዲሪ ቆንስላ ጄነራል ጽህፈት ቤት ቆንስል ጄኔራል አቶ ፈቃዱ በየነ ባስተላለፉት መልእክት በሚወዷት ሀገራቸው ሥም ተሰብስበው ሕዳሴ ግድቡን ለመደገፍ በመገኘታቸው ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
አቶ ፈቃዱ በጀርመን ሙኒክ በአካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለሕዳሴ ግድቡ የተለመደ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉና በቀጣይነት ይህንን ስብስብ ወደ መላው የኢትዮጵያ ቀን በማሳደግ በአንድነት ከሀገራቸው ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በመርሃግብሩ የተገኙት ኢትዮጵያውያን የዜግነታቸውን ድርሻ ለመወጣትና ሀገራቸውን ለመደገፍ በመገኘታቸው የዜግነት ክብር እንደሚሰማቸው በመግለጽ በሙኒክ አከባቢ ያለው የዳያስፖራ አባላት በሁሉም ዘርፍ ድጋፉን አጠክሮ በማስቀጠል ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር እንደሚያሳዩ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡