የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበት አዋጅ ፀደቀ


ሰኔ 18/2016 (አዲስ ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 34ኛ መደበኛ ስብሰባ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ /ማሻሻያ/ ረቂቅ አዋጅን አፅድቋል።

ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ በምክር ቤቱ የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ገዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሸዊት ሻንካ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

በተሻሻለው አዋጅ በፌዴራል ደረጃ በሚሰሩ ፕሮጀክቶች የካሳ ትመና ክፍያ እንዲሁም ተነሺዎችን መልሶ ለማቋቋም ስልጣንና ኃላፊነት ያለባቸውን አካላት በግልፅ ለይቶ ለመወሰን የሚያስችል ስርዓት ስለመዘርጋቱ ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቶች በጥራት እና ጊዜ ቆጣቢ በሆነ መልኩ እንዲከናወኑና ለሀገራዊ ልማት ያላቸውን አስተዋጽዖ ከፍ የሚያደርግ ድንጋጌ በአዋጁ ስለመካታቱም አስረድተዋል።

ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች በተመሳሳይ ወጪና ተቀራራቢ ጊዜ እንዲጠናቀቁ የሚያስችል አሰራር ያስቀመጠ አዋጅ እንደሆነም ተናግረዋል።

ተገቢ ባልሆነ የካሳ ይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱት የፍርድ ቤት ክርክርና የባንክ አካውንት እገዳ በፕሮጀክቶች ላይ ይደርስ የነበረውን የስራ መጓተት የሚቀንስ አዋጅ እንደሆነም በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ተገልጿል።

በምክር ቤቱ የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ በበኩላቸው ቀደም ሲል የነበረው የካሳ ክፍያ ስርዓት ለብልሹ አሰራሮች የተጋለጠ መሆኑንና የልማት ተነሺዎች ተገቢውን ካሳ እንደማያገኙ ጠቁመው የተሻሻለው አዋጅ የመንግስት እና የህዝብ ሀብት እንዳይባክን ያስችላል ብለዋል፡፡

አዲሱ አዋጅ በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚያመጣው ችግር እንደሌለና ተገቢ ካሳ ያላገኘ አካል እስከ ላይኛው የፍትህ ተቋም በመሄድ መብቱን ማስከበር እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን የተሻሻለው አዋጅ ቀደም ሲል የነበረውን ብልሹ አሰራር በመቅረፍ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀትና ጊዜ እንዲጠናቀቁ ያግዛል ብለዋል፡፡

ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ የሚነሱ አለመግባባቶች ወደ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከሚመጡ እዚያው ባሉበት ፍርድ ቤቶች ቢታዩ የሚሉ አስተያየቶችም መነሳታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች የካሳ ክፍያ ለማከናወን አቅም ላይኖራቸው እንደሚችል ለቀረበው ጥያቄ፤ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ሲታቀዱ ለክልሎች የሚመደበው በጀት ላይ የካሳ ክፍያን ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

በተሻሻለው አዋጅ የተፈጻሚነት ወሰን አዋጁ ከጸደቀ በኋላ ለሚሰሩት የካሳ ግመታዎችና ክፍያዎች ሲሆን ቀደም ሲል የካሳ ግመታ ተሰርቶ ያልተከፈላቸው የልማት ተነሺዎች ግን በነባሩ አዋጅ እንደሚስተናገዱ ተገልጿል፡፡

በመጨረሻም ረቂቅ አዋጁ በ4 ተቃውሞ እና በ6 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አዋጅ ቁጥር 1336/2016 ሆኖ ጸድቋል፡፡