የካቲት 28/2014 (ዋልታ) በኬኒያ ናይሮቢ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ የተሳተፉ የ175 አገራት ወኪሎች የፕላሰቲክ ብክለትን እ.ኤ.አ በ2024 ለማስቆም የሚረዳ ታሪካዊ ነው የተባለ አስገዳጅ ስምምነት ለመመስረት መወሰናቸው ተነግሯል።
የመንግሥታቱ አካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም እንደገለጸው ስምምነቱ የፕላስቲክ ብክለትን ለማስቆም የሚደረገውን ዓለም ዐቀፍ ጥረት ህጋዊ ከለላ በመስጠት ለተፈጻሚነቱ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ ፕሬዝዳንትና የኖርዌይ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ኤስፕን አይድ “የጉባኤው አባላት ዓለማችን ለመጠበቅ የሚያስችለውን ከፍተኛ ውሳኔ ወስነዋል” ማለታቸውን ስካይ ኒውስን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
የፕላሰቲክ ምርቶች እድገት እ.ኤ.አ በ1950 ከነበረበት 2 ሚሊዮን ቶን 2017 348 ሚሊዮን ቶን መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ። በመሆኑም ችግሩን ለመቆጣጠር አፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጠው ይህ ቁጥር በ2040 በእጥፍ እንደሚጨምር ይገመታል።
የፕላስቲክ ምርቶች መሬት ውስጥ በሚቀበሩበትና በሚቃጠሉበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ የአካባቢ ብክለት እንደሚያስከትሉ ይታወቃል።