የመንግሥት ሥራዎችን በዲጂታል መልክ ለመስራት የሚያስችሉ ማዕከላት ተግባራዊ ሊደረጉ ነው

ሚያዝያ 11/2014 (ዋልታ) የመንግሥት ሥራዎችን በዲጂታል መልክ ለመስራት የሚያስችሉ የሥራ ትስስር ማዕከላት በ6 ተቋማት ተግባራዊ ሊደረጉ ነው፡፡

የሥራ ትስስር ማዕከላቱ የመንግሥት ሥራዎች በግንኙነቶች ሳይቆራረጡ፣ ጊዜና ቦታ ሳያግዳቸው በዲጂታል መልኩ እንዲሰሩ የሚያደርግ አሰራር የሚተገበርባቸው ናቸው፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን እና በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጄክት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረጉ ናቸው፡፡

ፕሮጀክቱን በጨረታ ያሸነፈው አይ ኢ ኔትወርክ ሶሉሽን የሚሰራው ሲሆን በ120 ቀናት ውስጥ አጠናቅቆ ለማስረከብ ስምምነት አድርጓል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂ ያለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እውን ስለማይሆን በሁሉም የልማት ሥራዎች የግል ዘርፉ አጋር ብቻ ሳይሆን ባለቤትም እንዲሆን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

በዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀከት ስር በመተግበር ላይ ካሉት ሥራዎች ውስጥ የመንግሥት የሥራ ትስስር ማዕከል ልማት አንዱ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ሥርዓቱ የመንግሥት ተቋማት ሥራዎች ጊዜና ቦታ ሳይገድባቸው የሚከወኑበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሁለተኛው ምዕራፍ ትግበራ በ50 የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና ክልሎች ጭምር ተግባራዊ እንደሚደረግ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW