የመንግስታቱ ሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ የጠራው ስብሰባ ውድቅ እንዲደረግ የአፍሪካ አገራት ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ ቀረበ

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) የተባበሩት መንግስታት የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ የጠራው ስብሰባ ውድቅ እንዲደረግ የአፍሪካ አገራት እና የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ ቀረበ፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረቤት አገራትና የኢጋድ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍስሀ ሻውል እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ካሳዬ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም የፖለቲካ አጀንዳን ለማስፈፀም በማሴር ምክር ቤቱ በጠራውን ልዩ ስብሰባ ውድቅ እንዲደረግ አገራቱ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡
የአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ይዟቸው በነበሩ ቦታዎች የፈጸማቸውን አሰቃቂ ጭፍጨፋና የንብረት ውድመት በተመለከተ የጎረቤት አገራትና የኢጋድ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍስሀ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አንዳንድ ምዕራባውያን አገራትና የመገናኛ ብዙኃን ሀሰተኛ ዘገባዎችን በማሰራጨት በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት ወደ ጎን በመተው የሽብር ቡድኑን የሚደግፍና የአገሪቱና ገጽታ የማጠልሸት እንቅስቃሴን እየገፉበት እንደሆነም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

የዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ካሳዬ በበኩላቸው አፍሪካውያን የውስጥ ጉዳዮቻችንን በራሳችን የመፍታት አቅም ያለን በመሆናችን የውጭ ጣልቃ ገብነትን በጋራ መቃወም ይገባናል ብለዋል።

በርካታ የአፍሪካ አገራት የበቃ #NoMore ዘመቻን በመቀላቀላቸው አመስግነው ያልተቀላቀሉም እንዲቀላቀሉ ለአምባሳደሮቹ ጥሪ መቅረቡን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡