የመካላከያ ሚኒስቴር የድል መግለጫ

ነሐሴ 29/2013 (ዋልታ) – በምእራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የሕወሓት የሽብር ቡድን ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን የመካላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢፌዴሪ መካላከያ ሚኒስቴር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት በመከላከያ ሰራዊት የሰራዊት አቅም ግንባታ አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ የሽብር ቡድኑ አራት አርሚዎች እንዳሉት በመግለጽ፤ አርሚ አንድ ብሎ የሰየመውና በከሃዲው ጀነራል ምግበ የሚመራው በሁመራ አካባቢ ደባርቅ እና ዳባትን በመቁረጥ ጎንደርን ለመያዝ ቢፈልግም ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን ተናግረዋል፡፡
አርሚ 1 በአጠቃላይ 9 ክፍለ ጦሮች የነበሩት ሲሆን ሙሉ በሙሉ መደምሰሳቸውን ነው የገለፁት።
የሽብር ቡድኑ ወደ ሱዳን መውጫ መንገድም ሙሉ በሙሉ እንደተዘጋበት ሌተናል ጀነራል ባጫ አሳውቀዋል።
አርሚ 2 የሚባለው እና በከሃዲው ሜጀር ጀነራል ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ የሚመራው ኃይል በጋሸና ከክምር ድንጋይ ጀምሮ በተደረገ ውጊያ ሁለቱ ክፍለጦሮች ተደምስሰውበታል ሲሉም አክለዋል፡፡
በተጨማሪም ከውጭ በብርጋዴል ጀነራል ፍስሃ የሚመራ እና የሰለጠነ በሽንፋ በኩል ከቅማንት ቅጥረኛ ቡድን ጋር በመተባባር ጥቃት የሰነዘረው አርሚ 3 ሲደመሰስ የተረፈው ወደመጣበት ፈርጥጧል ብለዋል።
ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁም ብለዋል፡፡
በትዝታ መንግሥቱ