የመደመር የውጭ ጉዳይ እሳቤ

መደመር

የመደመር የውጭ ጉዳይ እሳቤ

(የአፍሪካ ቀንድ አንድምታ)

መግቢያ እንደ መንደርደሪያ

የአፍሪካ ቀንድ አገሮች በባህል፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ እና በድንበር መጋራት ሊገለፅ በሚችል መልኩ እርስ በርስ በጣም የተጠላለፉ ናቸው። የአፍሪካ ቀንድ በዓለም ላይ ካሉት የፖለቲካ ተለዋዋጭ አካባቢዎች አንዱ ነው። የአፍሪካ ቀንድ በዓለም የተወሳሰቡና የግጭት አካባቢዎች ከሚባሉት አንዱ ሲሆን፤ የቀጣናው አገሮችም ለረጅም ዘመናት በፖለቲካ ችግሮች ውስጥ የኖሩና ያሉ፣ በአካባቢያዊና አገራዊ ተቃውሞዎች የሚፈተኑ፣ በውስጣዊ እና ቀጣናዊ የእርስ በእርስ አመፃና ፉክከር የሚናጡ መሆናቸው ይገለፃል።

ቀጣናው ለረጅም ዓመታት የስትራቴጂካዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ የኃይል ሽሚያ መድረክ ሆኖ የኖረ ሲሆን፤ በምሳሌነት የሚጠቀሱት ዋና ዋናዎቹ የቅርብ ጊዜ ክስተቶችም የሁለተኛው የዓለም እና የቀዝቃዛው ጦርነቶች ተፎካካሪዎች በቀይ ባሕር እና የግብፅ በአባይ ውኃ ላይ የበላይ ለመሆን ሲያደርጉት የቆዩት ሽኩቻ፣ እንዲሁም የአሜሪካ አስተዳደር በሽብርተኝነት ላይ የከፈተው ዓለም አቀፋዊ ጦርነት አንድ ቀጣና መሆን ለአፍሪካ ቀንድ ፈተና ሆነው መዝለቃቸውን ይዘረዝራል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የዓለም ኃያላን እና ሌሎች ጠንክረው በመውጣት ላይ ያሉ የተለያዩ አገራት በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር አካባቢዎች የጦር ሰፈር የመገንባት ውድድር ውስጥ መግባታቸው፤ ቀጣናው የተለያዩ አካላት የመወዳደሪያ መድረክ መሆኑን የሚያሳይ ሌላ ማስረጃ ነው። ከነዚህ ችግሮች ጋር ተያይዞም በቀጣናው እንደ ሽብርተኝነት፣ ስደት፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ያሉ ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮችም አካባቢውን ሲያምሱት ይታያል፡፡

ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አገራት በበለጠ ዓለም አቀፍ ድንበሮችን የምትጋራ አገር ስትሆን ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያን ይከተላሉ። ይህ የሚያመለክተው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰቱ ጉዳዮች በአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ተፅእኖ እንደሚኖራችው ነው። ይህ የሆነበት ምክንያትም አገሪትዋ ባላት ታሪካዊ፣ ጂኦግራፊያዊ እና ሥነ ህዝባዊ ባህርያት እንዲሁም በአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት ዋና ተዋናይ እና ንቁ ተሳታፊ መሆንዋ ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ ጥንታዊ ሀገሮች አንዷ ከመሆኗም በላይ ከአውሮፓውያኑ ቅኝ ግዛት ራሷን በመከላከል ነፃነቷን ጠብቃ ቆይታለች። አገሪቱ በዓለም ዙሪያ ካሉ በርካታ ግዛቶች ጋር ረጅም ጊዜ የውጭ ግንኙነት ታሪክ ያላት እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች የሚጠቆሙ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረው በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት የተለያዩ አገራት ተወካይ ቆንስላዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ነበር።

የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማም ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥም ሆነ በአካባቢው ላይ የምታደርጋቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እና የምትወስዳቸው ርምጃዎች በቀጣናው አጠቃላይ ልማት፤ ሰላም እና ደህንነት ላይ ትልቅ ተፅእኖ የሚያሳርፉ ጉዳዮች የመሆናቸውን ጉዳይ መሰረት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመጋቢት 24 2010 ዓ.ም ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የመደመር የውጭ ጉዳይ እሳቤ ሃሳብ ላይ ተመስርቶ በዋናነት በእሳቸው መሪነት እየተተገበረ የሚገኘው የተሻሻለው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ አካሄድ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያለውን አንድምታ ለመገምገም መሞከር ነው።

የለውጥ እና ቀጣይነት ባህርይ

አብዛኛውን ጊዜ የአገሮች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በለውጥ እና ቀጣይነት ባህርይው ይታወቃል፡፡ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በዙሪያው ካሉ አጎራባች አገሮች ጋር ያላት የውጫዊ ስጋቶች ከፍተኛ ተፅእኖ ያለበትን የውጭ ግንኙነት የሚመራበት ፖሊሲም ይህ ባህርይ ይስተዋልበታል። በተለያዩ ጊዜያት የመጡ የኢትዮጵያ መሪዎችም በአፍሪካ ቀንድ የነበራቸውን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በለውጥ እና ቀጣይነት መርህ ተመስርተው በማስተካከል በጊዜያቸው የተፈጠሩ ውጫዊ ስጋቶችን ለመቅረፍ እና ቀጣናዊ ትብብር እና ውህደት ለማምጣት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ ያለፉት አራት ተከታታይ መሪዎችም (የአፄ ኃይለስላሴ፣ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ) የነበሩባቸው ጊዜያትም እነዚህ ጉዳዮች የተለያዩ መልኮች ይዘው ሲከሰቱ ተስተውለዋል።

ከላይ ከተጠቀሱት መሪዎች መካከል የመጀመሪያዎቹ ሁለት መሪዎች ትኩረታቸው ውጫዊ ጉዳዮች ላይ የነበረ ሲሆን፤ የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ደግሞ ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ሲንሳቀሱ የነበሩ መሪዎች ነበሩ፡፡ ትኩረትን በውጫዊ ጉዳይ ላይ ማድረግ ማለት የኢትዮጵያ ዋነኛ የብሄራዊ ደህንነት የስጋት ምንጭ ውጫዊ መሆኑን በማመን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አካሄድ እና አቅጣጫን መመስረት ሲሆን፤ ትኩረትን በውስጣዊ ጉዳይ ላይ ማድረግ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የደህንነት ስጋቶች እንደ ፖለቲካዊ (የዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር) እና ኢኮኖሚያዊ (ኢኮኖሚያዊ ኋላ-ቀርነት እና ድህነት) ችግሮች ያሉ ውስጣዊ ተጋላጭነቶች እና ተግዳሮቶች መሆናቸውን በማመን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አካሄድ እና አቅጣጫን መወሰን ነው።

ይህ ሂደትም ቀጥሎ የአሁኑ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ በመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤ ላይ የተመሰረቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ለውጦች ታይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአገሪቱን ከፍተኛ ስልጣን ከያዙ በኋላ በተለያዩ አጋጣሚዎች ደጋግመው የሚያወሱት የመደመር የአመራር እሳቤያቸውን ጠቅለል ባለ አኳኋን በተነተኑበት፣ በልዩ ልዩ የፖለቲካ እና የመንግስት ጉዳዮች ላይ ያላቸው ሃሳብ እንዴት ሊተገበር እንደሚችል ባመላከቱበት፣ ከዚህም በዘለለ የአስተዳደራቸውን ቀጣይ አቅጣጫዎች በተመለከተ አቅጣጫ በሰጡበት የ”መደመር” መጽሐፍ ውስጥ ዓለም አቀፍ አዝማሚያዎችን እና አገራዊ አንድምታቸውን በመገምገም የመደመር የውጭ ግንኙነት አቅጣጫቸውን ገልጸዋል።

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አገራችን የአቅም ክምችት ከፈጠረችባቸው መስኮች አንዱ እና ዋነኛው እንደሆነ ጠቁመው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የለውጥ እና ቀጣይነት ባህርይውን በመጠቀም መልካም ነገሮችን በማስቀጠል እና ከወቅታዊ ሁኔታዎች አንፃር መሻሻል ያለባቸው ነገሮችም በማሻሻል የአገሪቱን ውጭ ግንኙነት አቅጣጫ ለወቅታዊ አካባቢያዊ እና ዓለማዊ ቁመና የሚመጥን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት በሚመሰረትበትና በሚጠናክርበት ጊዜ በጠጣር ብሄራዊ ኃይል (Hard Power) ላይ ከመመስረት ይልቅ በገር የኃይል አማራጮች (Soft Power) ላይ መመስረት እና ለዚህም ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አሁን ዓለም ለሚጠይቀውና ኢትዮጵያ ለምትፈልገው የትብብር ግንኙነት ምቹ እንደሆነ ያመላከቱ ሲሆን፤ ፉክክርን እና ትብብርን አስታርቆ የሚጓዝ፣ ጥቅምን ሳይሆን ግንኙነትን ያስቀደመ፣ ከአንፃራዊ ጥቅም ይልቅ ለፍፁማዊ ጥቅም ትኩረት የሰጠና ከአሉታዊ ፍረጃ ነፃ የሆነ መሆን እንዳለበት አስቀምጠዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ግንኙት ሥራዎቻችን ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በተመለከተ ሲገልጹ፤ “ጎረቤት አገራትን የማስቀደም እና ብሔራዊ ክብርን ከፍ የማድረግ” ጉዳዮች ትኩረት እንደሚሰጣቸው ገልፀዋል። ከጎረቤት አገራት ጋር በተገናኘ በደህንነት ስጋት ላይ ከተመሠረተ ግንኙነት ወጥቶ በምጣኔ ሃብታዊ ትብብር እና በውህደት ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ የሚሞግቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ እሳቤ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተይዞ የቆየውን የአረብ አገራትን እንደ ችግር እና ታሪካዊ ጠላት የመመልከት ዝንባሌ ተስተካክሎ አገሮቹን እንደ አካባቢያዊ አጋር ማየት እንደሚገባ መክረዋል።

ሌሎች የመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤን የገመገሙ የተለያዩ የቀጣናውን ጉዳይ የሚከታተሉ ተንታኞች እንደሚገልፁት፤ የመደመር የውጪ ግንኙነት እሳቤ መሠረቱ የአገር የህልውና ጥያቄ እንደሆነ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤ ኢትዮጵያ በታሪኳ በቀጣናው፣ በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስትጫወት በነበረው መልካም የውጭ ግንኙነት ስራዎች ላይ የነበሩ ትልልቅ ሚናዎች እና የዲፕሎማሲ መስክ ውጤቶችን ለማሳደግ የሚሰራ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

መደመር ቀጣናዊ ትብብርን ያማከለ የኢኮኖሚ ትስስርን እውን ለማድረግ ይሰራል ብለው እንደሚያምኑ የሚጠቅሱ ወገኖች ደግሞ፤ መደመር ከውጪ ግንኙነት አንፃር ከጎረቤት አገራት ጋር ያለ ግንኙነትን ማሻሻል እና ማጥበቅን በማስቀደም አካባቢያዊ የጋራ የእድገት እና ብልፅግና ዓላማ እንዳለው ያመለክታሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ አሁናዊው የዓለም አቀፍ ስርአት በሽግግር ላይ የሚገኝ ሲሆን ስርአቱ በተለይ ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ ታዳጊ አገሮች የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መልካም እድሎችና ፈተናዎች እንዳሉት በመግለፅ፤ እነዚህን መልካም እድሎች ለመጠቀም እና ፈተናዎችን ደግሞ ለመቀነስ ከሌሎች አዳጊ አገሮች ጋር በጋራ መንቀሳቀስን ያለመ አካሄድ የሚከተል ፖሊሲ ነው ብለው እንደሚያምኑ ይገልፃሉ።

የመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤ ላይ በመመስረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከፍተኛ ውጤት ያመጡባቸውን በቀጣናው የተሰሩ የውጭ ግንኙነት ስራዎችን በዋናነት በአራት መክፈል የሚቻል ሲሆን፤ እነሱም ጎረቤት አገራትን ያስቀደሙ የውጭ ግንኙነት ስራዎች፣ የኢትዮ-ኤርትራ ስምምነት መታደስ፣ አዳዲስ ጉዳዮችን ያካተቱ የውጭ ግንኙነት የስምምነት ማእቀፎች እና በቀይ ባህር ጉዳይ ላይ ተይዞ የነበረው የአገሪቱ የቀዘቀዘ አቋም መለወጥ ናቸው። ከዚህ አንፃር ዋና ዋናዎቹ ውጤቶችም ከዚህ የሚከተሉት ናቸው።

ጎረቤት አገራትን ያስቀደመ የውጭ ግንኙነት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን እንደመጡ የመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤያቸው እና በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዙሪያ ለሚመለከታቸው አካላት ስልጠናና የተልዕኮ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡ በመቀጠልም ወደ ሁሉም የቀጣናው ጎረቤት አገራት ጉዞ በማድረግ ከአገራቱ ጋር የነበሩ ግንኙነቶችን የማደስ እና የማጠናከር ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ በዚህም ቅድሚያ የሚሰጡት ጎረቤት አገራትን ለሚያስቀድሙ በወንድማማችነት መንፈስ ላይ ለሚመሰረቱ የውጭ ግንኙነት ስራዎች እንደሆነ አሳይተዋል።

በውጭ ግንኙነት ስራዎች ውስጥ የጎረቤት አገሮች ጉዳይ በብዙ ረገድ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ሲሆን፤ እሳቸውም ይህን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ለአካባቢያዊ ጉዳዮች ቅድሚያውን ሰጥተው የውጭ ግንኙነት ስራዎችን ሲመሩ ታይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የመጀመሪያ የውጪ ጉዟቸው ወደ ጅቡቲ ነበር። ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ካላት ስትራቴጅካዊ ጥቅም ባሻገር ሁለቱ ሀገራት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለመፍጠር ከፍተኛ ፍላጎት ሲያሳዩ ተስተውለዋል። የጅቡቲ ወደብ ለብዙ ዓመታት ወደብ ለሌላት ኢትዮጵያ ዋነኛው የባህር በር ሆኖ የቆየ ሲሆን፤ እሳቸው ከመጡ በኋላ በይፋ ስራ የጀመረው በቻይና የተሰራውና 756 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የኤሌክትሪክ የባቡር መንገድ ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ያላትን ጠቀሜታ ከፍ አድርጎታል።

ሁለተኛው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ወደ ሱዳን ያቀና የነበር፡፡ በዋናነትም በተለያዩ የፖለቲካ፣ የደህንነት፣ የኢኮኖሚ እና የድንበር ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የሁለትዮሽ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ውይይቶች እና ስምምነቶችም ተደርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከክልላዊ ጉዳዮች በተለይም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ተከታታይ ውይይቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። በቅርቡ ወደ ሱዳን ባደረጉት ጉዞም የሱዳን ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች የውይይቱ ዋነኛ አጀንዳ ነበሩ፡፡

ሱዳናውያን ከውጭ ጣልቃ ገብነት በፀዳ መንገድ የፖለቲካ ችግራቸውን እንዲፈቱ ማድረግ ሌላኛው የውይይታቸው አጀንዳ እንደነበር በተለያዩ ሚዲያዎች ሲገለጥ ነበር። ሱዳናዊያን ካለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የፖለቲካ ችግራቸውን መፍታት ስለሚችሉበት ሁኔታ ከመንግስት ተወካዮች እና ከተለያዩ የሱዳን የነፃነት እና እኩልነት ኃይሎች ጋር የተወያዩ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የጋራ ድንበራቸውን ጉዳይ በሰላም ለመፍታት ስለሚችሉበት ሁኔታ ውይይት አድርገዋል፡፡

በሌላ በኩል የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን በሞቃዲሾ ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግስት ጋብዘው ከተወያዩ በኋላ የሁለቱ አገራት መሪዎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታን ጨምሮ ሁለቱን አገራት በሚያገናኙ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመተባበር ቃል የገቡበት የጋራ መግለጫ አውጥተዋል። የባህል ልውውጥን ለማሳደግ እና የቪዛ አገልግሎቶችን ለማስፋፋትም ተስማምተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሶማሊያው ፕሬዚዳንትና ራሷን ነፃ አገር አድርጋ ባወጀችው ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንቶች መካከል መቀራረብን ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፤ በተለያዩ የአገሮቹ እና ሌሎች ውጫዊ ምክንያቶች የተነሳ የሚፈለገውን ውጤት ሳያመጣ እስከ አሁን ድረስ ቆይቷል።

ይሁንና እ.ኤ.አ በየካቲት 2020 አዲስ አበባ ውስጥ የተካሄደውን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን ተከትሎ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ ፋርማጆ እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲን በጽህፈት ቤታቸው ጋብዘው አነጋግረዋቸዋል። በዚህ ጊዜም የሶማሊያው ፕሬዝዳንት እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ ሶማሌላንድ ውስጥ ስለተፈጸመው ጭፍጨፋ ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን፤ የሶማሌላንዱ ፕሬዝዳንትም የቀረበውን የይቅርታ ጥያቄ ተቀብለዋል፡፡

ሌላው ወደ ጎረቤት አገር ያደረጉት ጉብኝት በኬንያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት እና ንግድ ለማጠናከር በማሰብ ወደ ኬንያ ያደረጉት ጉብኝት ሲሆን፤ በዚህም ወቅት ሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር፣ የአካባቢውን ፀጥታና ሰላም በማስጠበቅ ረገድም ቁልፍ አጋርነታቸውን ለማስቀጠል ተስማምተዋል። በተጨማሪም በቀጣናው ሽብርተኝነትን በመዋጋት እንዲሁም ሶማሊያን ወደ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በበለጠ ቁርጠኝነት በጋራ ለማከናወን እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ላሉ ተግዳሮቶች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በሚደረገው እንቅስቃሴ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

በዚህ ወቅት ሶማሊያ እና ኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ ላይ ነበሩ፡፡ ይህም ሁለቱ አገራት በሚጋሩት የባህር ድንበር ላይ ካለው አወዛጋቢው የጋዝ ክምችት ይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ነበር። በወቅቱም የሁለቱ አገራት መንግስታት እንዲወያዩ እሳቸው ባደረጉት ጫና መነሻነት ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ፋርማጆና ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በናይሮቢ የተገናኙ ሲሆን፤ በአገራቱ ላይ ለተፈጠረው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር መፍትሄ ለማምጣትም ተወያይተዋል። ይህንንም ተከትሎ የሶማሊያ መንግስት ባወጣው መግለጫ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሁለቱን መንግስታት ውይይት በማሳለጥ ለነበራቸው ሚና እናመሰግናለን” ብሎ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ሂደት ትልቅ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል። በዚህም የተነሳ የደቡብ ሱዳን መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን እያደረጉት ያለውን ጥረት አድንቋል። እሳቸው ወደ ስልጣን ሲመጡ የአንድነት ራእይ ይዘው የመጡት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናውም ጭምር እንደሆነ እና የመደመር የውጭ ጉዳይ እሳቤያቸውን በማንሳት በተለያዩ ሚዲያዎች ሲገለፅ ቆይቷል።

የኢትዮ-ኤርትራ ስምምነት መታደስ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተሾሙ የመጀመሪያው ቀን ለኤርትራ የሰላም ጥሪ ማቅረባቸው በበርካቶች ዘንድ ያልተጠበቀ ነበር። በጊዜው የአፍሪካ ቀንድ በተለያዩ ኃይሎች ፍላጎት ከመቼውም ጊዜ በላይ ውስብስብ መጠላለፍ ውስጥ እንዳለ ጠቁመው በባህል፣ በቋንቋና በታሪክ የተሳሰሩት ሁለቱ አገራት ወደ ስምምነት ሊመጡ እንደሚገባ ተናግረዋል። በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግርም “በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ አገራት ህዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነታችንን በጋራ ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለፅኩ፣ የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለው” ብለዋል። ይህንንም ባሉ በተወሰኑ ቀናት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሻሻል እና ሁለቱን አገራት ለማስታረቅ ታሪካዊ ጉብኝታቸውን ወደ አስመራ አድርገዋል።

በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግርም የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ቀድሞ ሁኔታው መመለሱ እና ኤምባሲዎች መከፈታቸውን፣ ቀጥተኛ በረራዎችም መጀመራቸውን እና በሂደት የቀሩትን ትንንሽ ጉዳዮችን እንደሚፈቱ ገልፀው ነበር፡፡ የሚያስቡትን ግንኙነት ጥንካሬ ለመግለጽም ፕሬዝዳንቱ ከፈቀዱ የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኜ አገለግላለሁ” ሲሉም ተደምጠዋል። ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ጉዳይ ሰው ሰራሽ እንደሆነና በአገሮቹ ወንድማዊ ግንኙነት ውስጥ ሁለተኛው ጉዳይ መሆኑን ገልፀው ነበር።

በወቅቱም ስምምነቱ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ደህንነት ዙሪያ የታየ የመሰረታዊ ለውጥ መጀመሪያ ሊሆን ይችላል በማለት አካባቢውን የሚከታተሉ ተንታኞች ሲገልፁ ከማየታችንም በላይ እርሳቸውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ የኖቤል የሰላም ኮሚቴ ሊቀመንበሯ በሽልማት ሥነ ስርአቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀውን ውዝግብ በሰላም ለመፍታት ባሳዩት ተነሳሽነት፣ በኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ግንባታ ለተጫወቱት ሚና እንዲሁም በኢትዮጵያ፣ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ሰላምና እርቅ እንዲመጣ ባደረጉት አስተዋፅኦ እ.ኤ.አ የ2019 የኖቤል ሰላም ተሸላሚ እንዲሆኑ መመረጣቸውን አስታውቀዋል።

አዳዲስ የስምምነት ማዕቀፎች

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መርሆዎች የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ጥቅም የሚያስጠብቁና የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚያስከብሩ፣ በጋራ ጥቅምና በእኩልነት እሳቤ ላይ የተመሰረቱ፣ ከጐረቤት አገሮች እና  ከሌሎች  የአፍሪካ እና ሌሎች አዳጊ አገሮች ጋር በየጊዜው እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚያዊ ህብረትና የህዝቦች ወንድማማችነትን ማጐልበትን ማእከል ያደረጉ ሆነው ለረጅም ጊዜ ቆይተዋል፡፡ ባጠቃላይ ኢትዮጵያ የነበራት የውጭ ግንኙነትም በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ ሆኖ ለረጅም ጊዜ የቆየ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤ ማእቀፍ የተደረጉት የስምምነት ማእቀፎች ግን ከዚህም ላቅ ያሉና አዳዲስ ጉዳዮችንም ያካተቱ ነበሩ።

ከዚህ ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው ጉዳይ በመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤ ማእቀፍ ውስጥ የተገለፀው የአገሪቱን ብሄራዊ ክብር ለማረጋገጥ እና የዜጎችን ደህንነት እና ክብር አስጠብቆ ለመቀጠል የሚያስችል አለም-አቀፍ ይዞታ ለመፍጠር የተቀመጠው አቅጣጫ ነው፡፡ በዚህ አቅጣጫ ስርም አገራዊ ክብራችንን የሚፈታተነው እና ዜጎችን ለከፍተኛ ጉስቁልና እና ውርደት እንዲዳረጉ የሚደርገው አንዱ እና ዋነኛ ጉዳይ ስደት እንደሆነ የተቀመጠ ሲሆን፤ በዚህ በኩል ቀዳሚው ትኩረትም ዜጎች በስደት ውስጥ የሚገቡበትን መከራ ማስቆም እና የዜጎችን ክብር ማረጋገጥ መሆን እንዳለበት ተገልጿል፡፡

ይህን መነሻ በማድረግም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን እንደመጡ ያደረጓቸው የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ያለሙ በቀጣናው እና ከቀጣናው ውጭ የተደረጉ ጉብኝቶች አንዱ እና ዋነኛ አላማ የነበረው በሚጎበኙ አገራት ውስጥ በስደት የሚገኙ ዜጎች አጠቃላይ ሁኔታ ስለሚሻሻልበት መንገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገር ነበር፡፡ በዚህ መሠረትም ከተለያዩ አገራት ጋር የተለያዩ ስምምነቶችን መፈረም የተቻለ ሲሆን፤ በአገራቱ ለመኖር ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች እና ሌሎች ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ በአገሪቱ ያልተለመደ የውጭ ግንኙነት ስራን አሳይተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ለየት ያሉ ስምምነቶችን መፈራረም የተቻለ ሲሆን፤ ከጂቡቲ ጋር በተደረገው ውይይት የወደብ ድርሻ ለመግዛትና በምላሹም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ውጤታማ ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅቶችን የተወሰኑ ድርሻዎች ለመሸጥ የሚያስችሉ ሃሳቦች ቀርበው ከስምምነት ላይ መድረስ ተችሏል። ይህም ኢትዮጵያ ከፈተኛ ወጪ ከምታወጣበት የወደብ አገለግሎት ተጠቃሚ እንድትሆን በማድረግ የተረጋጋ የወደብ አገልግሎት ዋጋ እንዲኖር ከማድረጉም በላይ ቀስ በቀስ ይህ ድርሻ እያደገ ከሄደ በተለይ ከደህንነት አንፃር የሚኖሩ ውስንነቶችን ሊቀርፍ የሚችል ስምምነት ነው፡፡ ከሌሎች የቀጣናው አገሮች ጋር ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ግንኙነትን መፍጠር ከተቻለ ለቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር እና የውህደት ሃሳብ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነ የተለያዩ ተንታኞች ይገልፃሉ፡፡

በቀይ ባህርአቋም መለወጥ

ባለፉት አስርት ዓመታት በቀይ ባህር አካባቢ እና በክልሉ የሚዘዋወሩ የውሃ መስመሮች ላይ ከፍተኛ የጂኦ-ፖለቲካዊ ውድድር ትእይንት ሲስተዋል ቆይቷል። እነዚህ ጂኦ-ፖለቲካዊ ውድድሮች በፈጠሩት ግፊት ሳውዲ-አረቢያ እ.ኤ.አ. በ2020 የቀይ ባህር ምክር ቤትን አቋቁማለች። ስምንት አገሮችን (ሳውዲ አረቢያ፣ ግብፅ፣ ዮርዳኖስ፣ ኤርትራ፣ የመን፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያን) ያቀፈው ይህ የቀይ ባህር ምክር ቤት መቋቋሙም ቀጣናዊ መረጋጋትን ለመፍታት እንደ አንድ ማዕቀፍ ሊጠቅም ይችላል በማለት በተለያዩ አካላት ዘንድ በበጎ ሲጠቀስ ይስተዋላል።

በተቃራኒው ሌሎች ደግሞ ምክር ቤቱ በቀጣናው ውስጥ ቁልፍ የሆኑ እንደ ኢትዮጵያ፣ ሶማሌላንድ፣ ቱርክ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ያሉ ሀገራት ማግለሉን ከመጥቀስ በተጨማሪ ሌሎች ጉድለት የሚልዋቸውን ጉዳዮችን በማንሳት ሲተቹት ይስተዋላል፡፡ ከዚህ አለፍ ብለውም ይህ ማግለል ክልላዊ መረጋጋትን ለመፍታት ሊኖር የሚችለውን የምክር ቤቱን አቅም ይገድበዋል ብለው ሲገልፁም ይስተዋላል።

ለአብነት (አንዳንዶች እንደሚገልፁት በግብፅ ግፊት የተነሳ) ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል አለመሆኗ የቀይ ባህር ምክር ቤት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመቅረፍ አቀርበዋለው የሚለውን የቆመውን ድርድር የማስቀጠል አማራጭም የሚገድብ እንደሆነም ይገልፃሉ፡፡

በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ የሚከናወኑ ጉዳዮች በከፍተኛ ሁኔታ ተፅእኖ ከሚያሳድሩባቸው ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት። በሀገሪቱ ላይ በመርከቦች ጉዞ መታወክ እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ከሚፈጠረው የኢኮኖሚ ጫና በተጨማሪ የሀገሪቱ የኢንተርኔት መግቢያ በር (gateway) በቀጥታ ልንከላከለው በማንችለው መልኩ በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኝ በመሆኑ የደህንነት ፋይዳው የጎላ ነው።

ከዚህም ባሻገር ግብፅ እንዳቀደችው ኢትዮጵያን ከአካባቢው በማግለል አካባቢው ላይ የሚኖራትን ተፅእኖ አሰፋች ማለት ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት እና ደህንነት የሚኖረው አንድምታ ከፍተኛ ነው። እንዲህ ዓይነት ቀጣይ ስጋቶችን ከመቀነስ አንፃር ባለፉት አምስት ዓመታት ሲታይ የቆየው የባህር ኃይል የማቋቋም ፍላጎት እና እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴም ከመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤ ጋር ተያይዞ የሚጠቀስ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ቀዝቅዞ የቆየ የአቋም ለውጥ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመደመር መጽሐፋቸው በግልፅ እንዳስቀመጡት በውሃ ላይ ያለንን አቅም ከማስከበር ጋር የተያያዘው አንዱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ አገሪቱ በቀይ ባህር ላይ ያላት የኢኮኖሚዊ እና የብሄራዊ ደህንነት ጥቅም እንደሆነ ነው፡፡ ይህን ለማሳካትም ኢትዮጵያ ጠንካራ የሆነ የባህር ኃይል ግንባታ እንደሚያስፈልጋት አስቀምጠዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የባህር ኃይል ግንባታ በሀገራዊ ጥቅማችን ላይ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ተደማጭነታችንም ላይ ፈጣን ለውጥ ማምጣት የሚችል መሳሪያ በመሆኑ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሰራ የሚገባው ስራ እንደሆነም አስቀምጠዋል፡፡

በዚህ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ካቢኒያቸውን አዋቅረው ለካቢኒያቸው እርሳቸውና ሌሎች ሙያተኞች ስልጠና ከሰጡ በኋላ ለእያንዳንዱ ሚኒስትር መስሪያ ቤት የመጀመርያ የ100 ቀናት ስራን ሲሰጡ ለመከላከያ ሚኒስቴር ከተሰጡት ወሳኝ ስራዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ባህር ኃይልን ማቋቋም አንዱና ዋናው ነበር። ይህን መነሻ በማድረግም የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ስር እንዲቋቋም ተደርጎ ወደ ተለያዩ የዝግጅት እንቅስቃሴዎች እንዲገባ ተደርጓል፡፡

ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ በተለያዩ ጊዜያት እንደገለፁት የባህር ኃይልን አቅም በመገንባት ለነገው ትውልድ መሰረት የመጣል ስራ ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ እና እንደ አንድ የዚህ እቅድ ዋና ተግባርም የባህር ኃይል ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት መሰረተ ልማትን ለማሟላት የግንባታ ስራዎች በተለይ የመሰረታዊ ባህርተኞች ማሰልጠኛ ት/ቤት ግንባታ እንደተጀመረ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በአዲስ መልክ ከተመሠረተ ጀምሮ አባላቱ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ በማሠልጠን የተለያዩ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

እነዚህ ሁሉ በዋናነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሲከናወኑ የነበሩ የውጭ ግንኙነት ጥረቶች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው አገራት ልማት፣ ሰላም እና መረጋጋት ከፍተኛ አንድምታ ያላቸው ጉዳዮች እንደሆኑ በተለያዩ አካላት ሲገለፅ የቆየ ሲሆን፤ አንድምታቸውንም ኢኮኖሚዊ፣ ፖለቲካዊ እና የፀጥታ እና የደህንነት በሚል ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡

ኢኮኖሚያዊ አንድምታ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከመደመር አስተሳሰብ ሦስቱ ምሰሶዎች አንዱ የሆነው ክልላዊ ውህደት፣ ከዳበረ ዴሞክራሲ እና ኢኮኖሚያዊ ህያውነት ጋር ተያይዞ በቀጣናው ውስጥ የኢኮኖሚ መደጋገፍን በማምጣት ግጭቶችን የመቀነስ እድል እንዳለው ገልፀዋል። የቀጣናውም ሆኑ ሌሎች አገራት በተባበሩ ቁጥር በዓለም ላይ በአጠቃላይ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ የሚያጋጥሙ ግጭቶችም በቀጣይነት እንደሚቀንሱ ሲገልፁ ተሰምተዋል።

ይህን ሀሳባቸውን በምሳሌ ለማስረዳትም “ቶሎ መሄድ ከፈለግክ ብቻህን ሂድ፣ ሩቅ መሄድ ከፈለግህ ግን ከሌሎች ጋር ሂድ” የሚል አባባልን ተጠቅመው ሃሳባቸውን ሲገልፁ ተስተውለዋል፡፡ በዚህም መደመር እርስ በርስ መደጋገፍን እንደሚያመጣ እና እርስ በርስ መደጋገፍ ደግሞ በቀጣናው ውስጥ ሰላም እና ብልፅግናን እንደሚያመጣ ገልፀዋል።

ይህንን ለማሳካትም ኢትዮጵያ እንደ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (IGAD)፣ የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA) የመሳሰሉ ቀጣናዊ እንዲሁም እንደ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ስምምነት (CFTA) እና በአፍሪካ ህብረት (AU) ባሉ አህጉራዊ የንግድ ስምምነቶች እና ድርጅቶች እንዲሁም በሌሎች የተለያዩ የዓለም ድርጅቶች በንቃት በመሳተፍ ለራስዋ እና ለቀጣናው አገሮች የሚጠቅሙ እንቅስቃሴዎች ማድረግን አጠናክራ እንደምትቀጥል በተለያዩ ጊዜያት ሲገልፁ ተሰምተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከያዘችው የአካባቢ ማእከላዊ አቀማመጥ አንፃር በመደመር የውጭ ጉዳይ እሳቤ ላይ ተመስርቶ ከጎረቤት አገሮች ጋር እየተፈራረመቻቸው ያሉ የኢኮኖሚ በተለይም መሰረተ ልማት እና ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮሩ ስምምነቶች፤ ግንኙነቶችን በማጠናከር እና መደጋገፍንም በማምጣት በክልሉ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሁለንተናዊ ትስስር ለማምጣት ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡

ፖለቲካዊ አንድምታ

የተለያዩ ቀጣናውን የሚከታተሉ ተንታኞች እንደሚገልፁት፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የውስጥ እና የውጭ ጉዳዮች አካሄዶች ላይ እየታዩ ያሉት የለውጥ እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ እና በቀጣናው አገሮች መካከል ባለው ግንኙነት እንዲሁም በቀጣናው አጠቃላይ ፖለቲካ ላይ ከፍ ያለ አንድምታ ያላቸው እንደሆነ ነው። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ለረጅም ጊዜ እንደ የበላይ አስተባባሪ ስትታይ ብትቆይም ከተወሰኑ ጎረቤቶቿ ጋር ቅራኔ ውስጥ ሊያስገቡ የሚችሉ የተለያዩ ጉዳዮች የነበሩዋት አገር ነበረች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እነዚህን እና በሌሎች አገሮች መካከል የነበሩ ቅራኔዎችን ለመፍታት በወሰዷቸው ተነሳሽነቶች እና የማሸማገል ሚናዎች ከተለያዩ አካላት አድናቆትን አግኝተዋል፡፡ በነዚህ ጊዜያት ያደረጓቸው እንቅስቃሴዎች ለቀጣናው ፖለቲካዊ መረጋጋት፣ ሰላም እና ደህንነት ከፍተኛ የተስፋ ምልክቶች እንደሆኑ በተለያዩ ተንታኞች ሲገለፅ ቆይቷል። ኢትዮጵያ ከሌሎች የቀጣናው አገራት ጋር ባላት ሰፊ የድንበር ተጋሪነት የተነሳ ሲያካሂዷቸው የቆዩት ከጎረቤት አገሮች ጋር የተደረጉ የሁለትዮሽ እና የሶስትዮሽ ስምምነቶች እንዲሁም የተለያዩ አገራትን በማሸማገል ችግሮቻቸውን በስምምነት እንዲፈቱ ያደረጉዋቸው ጥረቶች በአካባቢው አገሮች መካከል የሚታየውን አለመተማመን ለመቅረፍ እና የአካባቢውን ፖለቲካዊ ትስስር አንድ እርምጃ ለማራመድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እየወሰዱት ያለው በቀጣናው አገሮች (ውስጥ እና መካከል) ያሉ ግጭቶችን የማሸማገል ተነሳሽነት እና እነዚህ አካላትም ችግሮችን ለመፍታት ያሳዩት ፈቃደኝነት መልካም ጅምሮች ቢሆኑም፤ አሁንም በአካባቢው የሚፈለገውን ፖለቲካዊ ትስስር ለማምጣት የቀጣናው አገሮች እርስ በርስ መተማመንን ማሳደግ፣ ከድንበር እና ድንበር ዘለል የተፈጥሮ ሃብቶች ባለቤትነት እና የአጠቃቀማቸው ሁኔታ ጋር የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ የስምምነት ማእቀፎችን በጋራ በማዘጋጀት እና ችግሮቹንም የሚመለከታቸውን አካላት በሙሉ በማካተት መፍታት እንዲሁም የውጭ ተፅእኖዎችን በጋራ መከላከል ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ስራዎችን የበለጠ አጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል፡፡

የፀጥታ እና ደህንነት አንድምታ

የቀጣናው አገሮች ውስጣዊ እና አካባቢያዊ ችግሮቻቸውን በውይይት ለመፍታት የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች የቀጣናውን አገሮች እና የዜጎቻቸውን ደህንነት ለሚያሰጉ የተለያዩ ግጭቶች እና ሌሎች ችግሮች አነስተኛ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ይመጣል። የኢትዮጵያ በመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤ ላይ የተመሰረተ ተስፋ ሰጪ ግንኙነት ለቀጣናው ህዝቦች ተስፋ የሚሰጥ እና በአካባቢውም መረጋጋትን፣ የጠበቀ ትስስርን እና ሰላምን የሚያመጣ እንዲሁም የቀጣናው አገሮችን ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች በጋራ ለመቅረፍ የሚያስችል ነው። ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ላይ የተመሰረተ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ የሚሰጥ አዲስ የትኩረት አቅጣጫ መጀመርዋ ለቀንዱ ሰላም እና መረጋጋት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ይህ አካሄድ በቀጣናው አገሮች ውስጥ የሚታዩ ክልላዊ የዲፕሎማሲያዊ ተግባራት ክፍተቶችን በማሻሻል ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ሊያደርግ የሚችል ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በነበራቸው ውይይት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተካሄደውን ጦርነት ቀስቃሽ የነበረውን የድንበር ጉዳይ ሁለተኛው ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ በፊት ወንድማማችነትን በሚያጠናክሩ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚፈልጉ መግለፃቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ‘የዘፈቀደ’ እና ‘ሰው ሰራሽ’ የቅኝ ግዛት ድንበሮች በሁለት እና ከዚያ በላይ በሆኑ አገሮች መካከል ሊኖር በሚገባው የጉርብትና ግንኙነት ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ሊሆኑ የሚገባቸው መሆኑን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በድንበር ምክንያት ግጭት ውስጥ ለሚገቡ ለቀጣናው እና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ትምህርት የሚሰጥ ጉዳይ ነው።

ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶች

በመደመር የውጭ ጉዳይ እሳቤ ላይ በመመስረት ኢትዮጵያ በቀጣናው ማካሄድ የጀመረቻቸው የተለያዩ የውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴዎች የተለያዩ ተግዳሮቶች ሲያጋጥሟቸው የቆዩ ሲሆን፤ እነዚህ ተግዳሮቶችም ውስጣዊ እና ውጫዊ ተብለው በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ሊከፈሉ የሚችሉ ናቸው፡፡

ውስጣዊ

አካባቢውን እና ኢትዮጵያን የሚከታተሉ ተንታኞች እንደሚገልፁት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በቀጣናው ሰላምን፣ መረጋጋትን፣ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን እና ብልፅግናን ለማምጣት የምታደርገውን እንቅስቃሴ የሚፈታተኑ ሁለት ዋና ዋና ውስጣዊ ተግዳሮቶች ያጋጠሟት ሲሆን፤ እነሱም በዋናነት የአገር ውስጥ ግጭቶች እና ጥራት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ያለመቻል ችግር ናቸው፡፡

የአገር ውስጥ ግጭቶች

የተለያዩ ቀጣናውን የሚከታተሉ ተንታኞች እንደሚገልፁት፤ ግጭት በአፍሪካ ቀንድ አገራት በሃሳብ ልዩነቶች አለያም በይገባኛል ጥያቄዎች ምክንያት በተለያዩ ማህበረሰቦች መካከል የሚፈጠሩ እና የተለመዱ ክስተቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የቀጣናው አገራት የቅርብ ጊዜ ታሪክ የሚያሳየው በውጫዊ ምክንያት ከሚፈጠሩ ግጭቶች ይልቅ በውስጣዊ ምክንያት የሚከሰቱ ግጭቶች አገራቱን የበለጠ እየጎዳቸው መሆኑን ነው፡፡ ሁሉም የቀጣናው አገራት ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ቢያንስ አንድ ጊዜ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገብተው ታይተዋል፡፡ ይህም የአፍሪካ ቀንድ ከየትኛውም የአፍሪካ አካባቢዎች በበለጠ የእርስ በርስ ጦርነቶችን ያስተናገደ አካባቢ እንዲሆን አድርጎታል። በቀጣናው የሚከሰቱ አብዛኛዎቹ ግጭቶችም ከአንዱ አገር ወደ ሌላ በቀላሉ የሚዛመቱባቸው የተለያዩ ምክንያቶች በመኖራቸው፤ በአካባቢው የሚፈጠሩ ግጭቶች በፍጥነት ሲሰፉ እና አካባቢያዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ሲይዙ ይታያሉ፡፡

በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡበትን ወቅት በምንመለከትበት ጊዜ በሁሉም ረገድ እጅግ ፈታኝ የሆኑ ውስጣዊ ጉዳዮች የበዙበት ወቅት ነበር። በዚህ ወቅት በሀገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ሲፈጠሩ የቆዩ የተለያዩ ግጭቶች መባባስ እና መስፋፋት ጀምረው የነበረ ሲሆን፤ ከለውጡ በኋላ በተወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎችም ችግሮቹን ለመቆጣጠር የሚቻልባቸው ሁኔታዎችን መፍጠር ተችሎ ነበር፡፡ ይሁንና በትግራይ ክልል የተፈጠረው ግጭት ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ ሁኔታዎች በሚያስደነግጥ መልኩ እየተባባሱ የቀጠሉ ሆንዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የመጣው የፖለቲካ አለመረጋጋትም በኢትዮጵያ በሁሉም ቦታዎች ያሉ ውስጣዊ ግጭቶች እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶቻቸው የከፉ እንዲሆኑ ሲያደርግ ከመቆየቱም በላይ ችግሩ በቀጣናው ሀገሮች መካከል ያለውን መተማመን እና መግባባት በማሻሻል ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሲደረጉ በነበሩ እንቅስቃሴዎች ላይ የራሱ የሆነ ጥላ አጥልቶበት አልፏል፡፡

የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት አለመቻል

ከኢኮኖሚያዊ ችግሮች ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት አስር ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበ ቢሆንም፤ የተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት የተረጋጋ እና ዘላቂ ሆኖ ምርታማነትን ያላሳደገ፣ አስተማማኝ የሆኑ በቂ የስራ እድሎችን መፍጠር ያልቻለ፣ በሚፈለገው ደረጃም ድህነትን መቀነስ እና ለዜጎችም የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ማምጣት ያልቻለ እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶች የሚታዩበት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢኮኖሚያዊ እድገቱ በነበረበት የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግር የተነሳ ኢኮኖሚው የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት፣ ኢ-ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲሁም የኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መሰረተ ልማቶች ጥራት ፈተናዎች ያሉበት ቀጣና ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ይህም ችግር ኢትዮጵያ በቀጣናው ልትወጣ የሚገባትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳትወጣ የራሱ የሆነ ተፅእኖ ሲያሳድርባት ይስተዋላል፡፡

ውጫዊ ተግዳሮቶች

በመደመር የውጭ ጉዳይ እሳቤ የተመሰረተውን የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴ የሚፈታተኑ ሌሎች ውጫዊ ሁኔታዎችም አሉ፡፡ እነሱም በዋናነት በቀጣናው የሚታየው የድንበር ተሻጋሪ ህገ ወጥ ጉዳዮች መስፋፋት፣ በጎረቤት ሀገራት ውስጥ የሚከሰቱ ውስጣዊ ግጭቶች፣ የሀገራት የእርስ በርስ ግጭቶች እና በቀጣናው ውስጥ ያለው የተለያዩ ውጫዊ አካላት ውድድር ናቸው።

የድንበር ተሻጋሪ ህገ-ወጥ ጉዳዮች መስፋፋት

ቀጣናው ባለው ጂኦ-ፖለቲካዊ እና ስትራቴጂካዊ ጥቅም እንዲሁም ግጭትን ጨምሮ ባሉት በርካታ ጥገኝነትን ለመፍጠር የሚያስችሉ አሉታዊ ምቹ ሁኔታዎች መበራከት የተነሳ ድንበር ዘለል ቀጣናዊ እና አለም-አቀፋዊ የሽብርተኛ ቡድኖች እንዲሁም የህገ-ወጥ ንግድ እና ስደት እንቅስቃሴዎች ከፍ ብለው የሚታዩበት አካባቢ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህም ብዙዎቹን የቀጣናው አገራት ለተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች ሲያጋልጣቸው ቆይቷል፡፡ ከዚህ ተጨማሪም እነዚህ ችግሮች ከሌሎች ችግሮች ጋር በመዳበል በቀጣናው አገራት መሃል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ጥርጣሬ የተሞላበት እና ግጭት የሚከሰትበት እንዲሆን ሲያደርጉት ይታያል፡፡

የጎረቤት አገራት ውስጥ የሚከሰቱ ውስጣዊ ግጭቶች

የጎረቤት አካላት ሰላምና ልማት መረጋገጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለአገራችን ሰላም እና ብልፅግና ቀጣይነት የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ሁሉ፤ በአካባቢያችን የተረጋጋ ሰላምና ልማት ያለመኖር ችግርም ለሀገራችን የብልፅግና ጉዞ መሰናክል መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ በተለይም ለአካባቢያዊ ውጫዊ ሁኔታዎች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ ይገኛል።

የቀጣናው የተፈጥሮ ሃብቶች ቀጣናውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከሚያስችሉ የተለያዩ እድሎች ውስጥ የሚመደቡ ሃብቶች እንደሆኑ ብዙዎቹን ያስማማ ሃቅ ቢሆንም፤ ቀጣናው ግን በነዚህ ሃብቶች የተነሳ ለበርካታ ዓመታት በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ሲታመስ ይታያል። እነዚህ የተፈጥሮ ሃብቶች አብዛኛውን ጊዜ ድንበር ዘለል እየሆኑ እና ሀገራትም የጋራ ሃብት መሆናቸውን በመቀበል በስምምነት መጠቀም የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ባለመፍጠራቸው፣ ለግጭት መነሻነት እና ማባባሻነት የሚኖራቸው አስተዋፅኦ ከፍ ያለ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ወሰኖች አሁንም በደንብ ያልተከለሉ በመሆናቸው ከወሰን እና ድንበር ጋር የተያያዙ ግጭቶች ከአስተዳደር ጋር በተያያዙ ግጭቶች እየተቀጣጠሉ ጠንካራ የእርስ በርስ ግጭት ምንጮች ሆነው ሲቀጥሉ ይታያል፡፡ የቀጣናው ደካማ የወሰን መስመሮች በአገር ውስጥ እና በአገራት መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች ወደ ቀጣናዊ ችግርነት ከሚሸጋገሩባቸው የተለያዩ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ሆነው ይገኛሉ፡፡ በዚህም በአንድ አገር ውስጥ የተፈጠሩ ግጭቶች ወደ ሌሎች አገሮች ሲዛመቱ እና የሌሎች አገሮችን የውስጥ ችግሮችንም ሲያወሳስቡ ይስተዋላል።

የአገራት የእርስ በርስ ግጭቶች

በቀጣናው ያሉ ድንበሮች በተገቢው አለመካለላቸው፣ ባልተካለሉ እና በተካለሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦች የሚጋሯቸው እንደ ውሃ እና የግጦሽ ሳር የመሳሰሉ የተፈጥሮ ሃብቶች እና የንግድ መስመሮች መኖር፣ በቀጣናው ሀገሮች ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መገባባት እና ለተቃዋሚዎች ድጋፍ መስጠት የተለመደ መሆኑ፣ የመንግስታት አቅም ሲዳከምም የሽብር እና ሌሎች ስጋቶች መጨመር እንዲሁም የቀጣናው አገሮች ከጎረቤቶቻቸው እና ከቀጣናው ውጭ የሚመሰርቷቸው ግንኙነቶች ግልፅ አለመሆን የሚፈጥሯቸው ስጋቶች በአገሮች መካከል ለሚፈጠሩ ግጭቶች መነሻ ሲሆኑ ይታያሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከአካባቢው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አንፃር የሌሎች አካላት አካባቢውን ለመቆጣጠር የመፈለግ ዝንባሌ እና ከዚህ ጋር ተያይዞ በነዚህ አካላት አማካኝነት አንዱን ወዳጅ ሌላኛውን ጠላት በማድረግ እና ሀገራቱን በተለያዩ ጥቅሞች በመደለል እና በማስፈራራት የሚፈጠሩ ግጭቶች በቀጣናው ጎረቤት አገራት መካከል መተማመን እንዳይኖር በማድረግ የቀጣናው አገራት ትብብራቸውን ለማጎልበት እና የአካባቢውን ሰላም እና መረጋጋት ለማሻሻል የሚደርጉት እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዳይሆን ሲያደርጉት ይታያል፡፡

የተለያዩ አካላት ፉክክር

የአፍሪካ ቀንድ ካለው ስትራቴጂካዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ጠቀሜታ የተነሳ የተለያዩ አካላት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ከሚወዳደሩባቸው የውድድር ቦታዎች አንዱ ሲሆን፤ ከውድድሩ መስፋት እና መወሳሰብ የተነሳም የነዚህ አካላት እንቅስቃሴያቸው እየጨመረ የመጣበት አካባቢ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እነዚህ የውጭ አካላት ተፅእኖ የሚፈጥሩባቸውን መንገዶች በሶሰት ዋና ዋና ክፍሎች ከፍለው የሚያስቀምጧቸው ሲሆን፤እነሱም ጥቅማቸውን አያስከብርም ወይም ከነሱ በተቃራኒ ቆሟል ያሉትን አካል በተለያዩ መልኮች አስወግዶ የስርአት ለውጥ በማድረግ፣ በህዝብ ግፊቶች እና በውስጣዊ ሁኔታዎች የመጡ ለውጦች እንዳይረጋጉ በማድረግ እና በጎረቤት አገራት መሃል ሽኩቻዎችን በመፍጠር ናቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮችም የቀጣናው አገሮች እንዳረጋጉ ማድረግ ከመቻላቸውም በላይ እርስ በርስ መተማመን እንዳኖራቸው በማድረግ ወደ ተለያዩ ግጭቶች ሲያስገቧቸው ይስተዋላል፡፡

ማጠቃለያ እንደ መውጫ

ባለፉት አምስት ዓመታት ውጤታማ ከሆኑት የአገሪቱ እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱና ዋነኛው “ጎረቤት አገራትን የማስቀደም እና ብሔራዊ ክብርን ከፍ የማድረግ” ቅድሚያ በሚሰጠው የሀገሪቱ የመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤ ላይ በመመስረት በዋናነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አማካኝነት የተከናወኑ ከአካባቢው ጎረቤት አገሮች ጋር የነበረን የአገሪቱ የውጭ ግንኙነትን የማደስ እና የማጠናከር ስራዎች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ በአፍሪካ ቀንድ ልማት፣ ሰላም እና መረጋጋት ላይ የምትፈጥረው ተፅእኖ ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የምታደርጋቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እና የምትወስዳቸው ርምጃዎችም በቀጣናው ላይ ትልቅ ተፅእኖ ያላቸው ሆነው ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ብዙ አካባቢውን የሚከታተሉ ተንታኞች በአሁኑ ጊዜ በቀጣናው ያሉትን ችግሮች በጋራ ለመፍታት አገራትን የማስተባበር እና የማስማማቱ ሥራ በብዛት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና በኢትዮጵያ ላይ ወድቋል የሚሉ ሲሆን፤ ይህ የአፍሪካ ቀንድን የማስተባበሩ ሥራም ከባድ መሆኑን ያስገነዝባሉ።

ኢትዮጵያ ቀጣናውን ለማስተባበር የመሪነት ድርሻ ልትወስድ ይገባታል የሚባልበት ዋነኛ ምክንያት አካላት ታሪካዊ ዳራ፣ የህዝብ ብዛት እና የገበያ ፍላጎት እንዲሁም ከያዘችው ማዕከላዊ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ እና የፖለቲካ ሚና አኳያ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቀጣናው መረጋጋት እና መልማት ወይም በሚፈጠሩ ግጭቶች እና ጣልቃ ገብነቶች ከሌሎች ከፍ ባለ ሁኔታ የምትጠቀም እና የምትጎዳ አገር በመሆንዋ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እንዲሳካ የጎረቤት አገራት ሰላም መሆን አለባቸው፡፡ ከዓለም አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ አንፃርም ከጎረቤቶች ጋር ተባብሮ መሥራት አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል። በመሆኑም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የገጠማትን ውስጣዊ ችግሮች በሂደት ተወጥታ ፊቷን ወደ እድገትና ልማት በመመለስ ለቀጣናው አገራት ውጤታማ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ትብብር የምትጫወተውን ሚና አጠናክራ መቀጠልዋ በእጅጉ አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል፡፡