የመጀመሪያው ዙር የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ክርክር ጆ ባይደን ደካማ አቋም ያሳዩበት ነበር ተባለ


ሰኔ 21/2016 (አዲስ ዋልታ) ትናንት ምሽት በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በተላለፈ የ2024 የመጀመሪያው ዙር የአሜረካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ክርክር በስልጣን ላይ ያሉት ጆ ባይደን ደካማ ሆነው የታዩበት እንደነበር ተነገረ።

በአንጻሩ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጠንከርና ሰከን ብለው መቅረባቸው ተዘግቧል።

የዲሞክራቲክ ፓርቲ እጩው ጆ ባይደን በምርጫ ክርክሩ ወቅት ሃሳብ ሲጠፋባቸውና ሲንተባተቡ የነበረ ሲሆን በእድሜያቸው ምክንያት ደከም ብለው ታይተዋል።

በዚህ የመጀመሪያ ዙር የምርጫ ክርክር ኢኮኖሚ፣ የስደተኞች ጉዳይ፣ ጤናና ታክስ ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች ሲሆኑ አንገብጋቢ ተብሎ የተጠበቀው የእስራኤልና ፍልስጤም ጦርነት ጉዳይ ትኩረት ተነፍጎት ታልፏል።

የ81 ዓመቱ ጆ ባይደን ባሳዩት ደካማ አጀማመር ለመሪነት ብቁ ስለመሆናቸው የዴሞክራቲክ ፓርቲ አመራሮችን እያሳሰባቸው መሆኑ ተጠቅሷል።

ሁለቱ ባላንጣ የፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ግለሰባዊ የሆኑ ጉዳዮችን እያነሱ ሲጎሻሰሙ ያመሹ ሲሆን ትራምፕ በጆ ባይደን መንተባተብ እና እርጅና ሲያላግጡባቸው አምሽተዋል። ፕሬዝዳንት ባይደን በበኩላቸው ትራምፕን ውሸታም እና ወንጀለኛ ሲሉ ጎንትለዋቸዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሁንም እውነት ያልሆኑ አስተያዬቶችን የሰጡ ሲሆን በአወያዩ በተደጋጋሚ የተጠየቋቸውን ጥያቄዎች በቸልታ ሲያልፉ ተስተውለዋል።

ለምሳሌ የ2024 ምርጫ ውጤትን በጸጋ ይቀበላሉ ወይ ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ “ነጻና ፍትሃዊ ከሆነ እቀበላለሁ፣ የ2020 ምርጫን የተሸነፍኩት በባይደን ተጭበርብሬ ነው” ብለዋል።

ሁለቱም ዕጩዎች በክርክሩ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ “እንደ ብዙ ፖለቲከኞች ይህ ሰው (ባይደን) እሮሮ ነው የሚያሰማው። የሚያደርገው ነገር ሁሉ በሚሊዮን የሚቆጠር ስደተኛ ወደ አገራችን እንዲጎርፍ በመፍቀድ አገራችንን አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ሲል ወቅሷል።

የሩሲያና ዩክሬን እንዱሁም የእስራኤልና ፍልስጤም ጦርነት መፈጠር ያልነበረበት ነው ያሉት ትራምፕ ይህም የባይደን ድክመት ነው ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።

አገራችን እየተፈረካከሰች ነው፤ ነገር ግን ይህ ችግር ከእንግዲህ አይቀጥልም። እንደገና ታላቅ እናደርጋታለን” ሲሉ ፎክረዋል የ78 ዓመቱ ዶናልድ ትራምፕ።

ባይደን በበኩላቸው በሳቸው የስልጣን ዘመን አሜሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እምርታ አሳይታለች ያሉ ሲሆን በተለይ በታክስ፣ በጤና ተደራሽነት እና ግሽበትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ስራዎች ሰርተናል ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።

የህዝብ አስተያየት መለኪያዎች እንደሚያሳዩት ምርጫ ክርክሩን የተመለከቱ 67 ከመቶ የሚሆኑት አሜሪካዊያን ዶናልድ ትራምፕ የትናንቱን ክርክር በበላይነት አሸንፈዋል ብለው እንደሚያምኑ የተጠቀሰ ሲሆን 33 በመቶ የመሆኑት የበላይነቱን ለጆ ባይደን ይሰጣሉ።

በቅድመ ክርክሩ ባይደን 55 በመቶ የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን ትራምፕ በበኩላቸው 45 በመቶ ክርክሩን በአሸናፊነት እንደሚወጡ ተገምቶ እንደነበር ተገልጿል።