የመጀመሪያ ዙር ፈተናቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደየአካባቢያቸው እየተመለሱ መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 3/2015 (ዋልታ) የመጀመሪያ ዙር የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና መጠናቀቁን ተከትሎ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ወደ የአካባቢያቸው እየተመለሱ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የመጀመሪያ ዙር የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ተፈታኞች ፈተናቸውን ከወሰዱባቸው የዩኒቨርሲቲ ማእከላት ነው ወደ የአካባቢያቸው እየተመለሱ ያሉት።

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ያለው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ለማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ከመስከረም 30 ቀን 2015 ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት መሰጠቱ ይታወቃል።

የማህበራዊ ሳይንስ ብሄራዊ ፈተና በትላንትናው ዕለት መጠናቀቁን ተከትሎ በሁለተኛው ዙር ፈተና የሚወስዱ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከጥቅምት 5/2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ የተመደቡበት የመፈተኛ ማዕከላት እንደሚገቡም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።