የሙስና ወንጀል በፈጸሙ አራት የፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ክስ ተመሠረተ

ፍትሕ ሚኒስቴር

ታኅሣሥ 4/2014 (ዋልታ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ ሕገ-ወጥ እስር በመፈፀም እና በማስገደድ 260 ሺሕ ብር የተቀበሉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ዐቃቤ ሕግ የሙስና ወንጀል ክስ መመሥረቱን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ክስ የተመሠረተባቸው አባላት በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የአስተዳደር ልማት ዘርፍ በሹፌርነት እና በጉዳይ አስፈጻሚነት የሥራ መደብ ላይ የሚሰሩት 1ኛ ረ/ኢ/ር ፍቃዱ ዘውዴ፣ 2ኛ. ረ/ኢ/ር ይስሀቅ ዳካ፣ 3ኛ ረ/ኢ/ር ደሴ ደጆ ዳዊት ዳዲ እና በልዩ ወንጀል ተካፋይነት ግብረ-አበር የሆነው ዳዊት ዳዲ ናቸው።

እነዚህ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ዲአፍሪክ ሆቴል አካባቢ የግል ተበዳይ በባለቤትነት በሚያስተዳድረው የንግድ መደብር በመግባት 4ኛ ተከሳሽ የመረጃ መረብ ደህንነት አገልግሎት ባልደረባ በመምሰል ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተከሳሾች የፌዴራል ፖሊስ አባልነታቸውን ሽፋን በማድረግ ምርመራ የማከናወን እና ተጠርጣሪ የመያዝ የሥራ ድርሻ ሳይኖራቸው እና ምንም ዓይነት ትዕዛዝ ሳይሰጣቸው የግል ተበዳይን በወቅታዊ ጉዳይ ትፈለጋለህ በማለት ለሥራ በተሰጣቸው መኪና ጭነውት ከወሰዱት በኋላ 1 ሚሊዮን ብር እንዲሰጣቸው ጠይቀው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባልቻ አባ ነፍሶ ቅርንጫፍ 260 ሺሕ ብር ወደ 1ኛ ተከሳሽ የቁጠባ ሂሳብ እንዲያስገባ በማድረግ ተከፋፍለዋል።

በዚህም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/07 አንቀፅ 9(2) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በፈፀሙት ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ክስ የቀረበባቸው መሆኑን የዐቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል።

በዛሬው ዕለትም ተከሳሾች በችሎት ቀርበው ክሱ የተነበበላቸው ሲሆን በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ለመጠባበቅ ለታኅሣሥ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መያዙን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኅብረተሰቡ መሠል ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን እንዲያጋልጥም ፍትሕ ሚኒስቴር ጥሪውን አቅርቧል።