መስከረም 12/2014 (ዋልታ) የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች “የነጭ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት” ዘመቻን ተቀላቅለዋል።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) “የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ይበልጥ አንድነታችን የሚጠናከርበት ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያን አንድነት በማስጠበቅና በሚነዙ አሉባልታዎች ባለመደናገር ጫናዎችን ለመመከት በጋራ መቆም እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማትም እንዲሁ የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ዘመቻ ተቀላቅለዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ልክ እንደ አድዋ ሁሉ ለኢትዮጵያ ህልውና በጋራ ትግል የምናደርግበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ ዜጎች በዚህ ዘመቻ ላይ በመቀላቀል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና የገንዘብ ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞች የ“ነጩ ፖስታ ለነጩ ቤተ-መንግሥት’’ ዘመቻን ተቀላቅለዋል፡፡
የህወሓት የሽብር ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች በንፁሃን ላይ እያደረሰ ያለውን ጥፋት አውግዘዋል፡፡
በዚሁ ንቅናቄ የተሳተፉት የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለማሳወቅ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም ተሳታፊ መሆን እንዳለበት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) አንስተዋል፡፡
“የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት” ንቅናቄ መስከረም 3/2014 የተጀመረ ሲሆን፣ እስከ መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚቆይ ይታወቃል፡፡