የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት

ግንቦት 30/2016 (አዲስ ዋልታ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 34ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
በዚህም፡-

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የ2017 በጀት አመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ የበጀት አዋጅ ላይ ነው፡፡ የ2017 ዓ.ም. የፌደራል መንግስት በጀት የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል የሆነውን የ2016-2018 የልማትና ኢንቨስትመንት እቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችን እና የ2017-2021 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና የፊስካል ማዕቀፍን ማስፈጸም እንዲቻል በሚያደርግ መልኩ ፤ የ2016 የፌደራል መንግስትን የፕሮግራም በጀት አፈጻጸም መነሻ በማድረግ፤ የመንግስት የፋይናንስ አቅም እና ተጠባቂ ገቢዎችን ታሳቢ በማድረግ እንዲሁም አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የተሰጣቸውን ተልኮና ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስፈልጋቸውን ወጪ በመገምገም እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡

በዚሁ መሰረት ለፌዴራል መንግስት መደበኛ ወጪዎች ፣ ለካፒታል ወጪዎች ፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ እና ተጠባባቂ ወጪን ጨምሮ ወደ አንድ ትሪሊየን የሚጠጋ በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው የፌዴራል መንግስት የ2017 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የአረንጓዴ አሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያ እና አስተዳደሩን ለመወሰን የወጣ አዋጅ ላይ ነው፡፡ በአረንጓዴ አሻራ የተጀመሩ ሰፊ ሥራዎች ቀጣይነትን ለማረጋገጥ፣ ሀገራችን ካላት የቆዳ ስፋት ከግማሽ በላይ የሆነው የተጎሳቆለ መሬት እንዲያገግም ለማድረግ፣ የደን ዘርፉ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዲሰጥ ለማስቻል፣ በአሁኑ ወቅት በተበጣጠሰ መልኩ በፌዴራል መንግስትም ሆነ በክልል መንግስታት ፋይናንስ እየተደረገ እየተሰራ የሚገኘውን የአረንጓዴ አሻራ ልማት በተቀናጀና ተገቢውን ሀብት መመደብ በሚያስችል የፋይናንስ አሰራር ስርዓት መደገፍ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት የአረንጓዴ አሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድን ማቋቋሚያ እና አስተዳደሩን ለመወሰን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

3. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ተቋማት ለሚሰጧቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚከፈሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመወሰን በቀረቡ ረቂቅ ደንቦች ላይ ነው፡፡ ተቋማቱ የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ አሰራሮችና የሰለጠነ የሰው ሀይል በማዘመን የአገልግሎት አሰጣጣቸውን የጥራት ደረጃ ማሻሻል ብሎም የተጠቃሚውን ማህበረሰብ አቅም ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት እንዲችሉ የሚያስችል ስርአት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ ደንቦቹ ተዘጋጅተው ቀርበዋል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውሉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡