የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት

ታኅሣሥ 1/2014 (ዋልታ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

መንግስት በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ይሁኝታ አግኝቶ ሲመረጥ ቃል ከገባባቸው አገራዊ ጉዳዮች መካከል ሁሉን አካታች የሆነ አገራዊ ምክክርና ውይይት በማካሄድ አገራዊ መግባባት እና በአገር ጉዳይ የጋራ አቋም እንዲኖር የሚያስችሉ ሥራዎችን መስራት አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት መሠረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ልሂቃንም ሆኑ ምልዓተ ሕዝቡ ተቀራራቢና በአገራዊ አንድነት ገንቢ አቋም እንዲይዙ ለማድረግ አካታች አገራዊ ምክክሩን ተግባራዊ ለማድረግ በገለልተኝነት ለመምራትና ለማስተባበር የሚችል ቅቡልነት ያለው ተቋም ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለውሳኔ ቀርቧል።

ምክር ቤቱም በቀረበው የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡