የማእድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ

ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና

የማእድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና ናቸው።

ስምምነቱ ከኢትዮጵያ ማዕድን ሀብትና ከዘርፉ ጋር የተጣጣሙ እንዲሁም በማዕድን ዘርፍ በከፍተኛነት የተለዩ የእውቀት ዘርፎችን በመለየት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኩል ስርዓተ ትምህርት እንዲዘጋጅላቸው እና ለባለሙያዎች እንዲሰጡ የሚያስችል ነው ተብሏል።

በማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ ዙሪያ በቀጣይነትም ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ ተጨማሪ አዳዲስ የትምህርት ዘርፎችን በማዘጋጀት መደበኛ ትምህርት እና አጫጭር ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ነው የተገለጸው።

ኢንጂነር ታከለ ኡማ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ብትሆንም፣ በሀብት ላይ መቀመጥ ለብቻው ሀብታም አያደርግም ብለዋል፡፡

ለዚህም ከምድር በታች ያለ ሀብቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እና የባለሞያዎችን አቅም በማጎልበት ያለውን ሀብት በአግባቡ መጠቀም መጀመር አለብን ብለዋል፡፡

ባለሙያዎች የትምህርት ዕድል ማግኘት በሚችሉበት መንገድ ዙሪያ የተደረገው ስምምነትም የዚሁ አካል መሆኑን ኢንጂነር ታከለ መናገራቸውን ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።