የማዕድን ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል ለልማት የሚውል 113 ሚሊየን ብር አበረከተ

ግንቦት 25/2014 (ዋልታ) የማዕድን ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል ጄህዲን ካሉብ እና ኤለሌ አካባቢዎች ላሉ ማኅበረሰቦች ልማት የሚውል 113 ሚሊየን ብር አበርክቷል ።
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ዛሬ ካሉብ ተገኝተው የገንዘብ ርክክብ ሲያደርጉ እንደተናገሩት በአካባቢው በሚከናወን የነዳጅ እና የጋዝ ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች በገቡት ስምምነት መሰረት ላለፉት አምስት ዓመታት ለማኀበረሰቡ የሚያስፈልጉ የልማት ሥራዎች በስምምነቱ መሰረት አልፈጸሙም፡፡
በመሆኑም የእነዚህን ዓመታት 113 ሚሊየን ብር ለክልሉ በማስረከብ የአካባቢው ነዋሪዎችና የክልሉ መንግሥት በመነጋገር በአካባቢው የተጓደሉ የልማት ሥራዎችን እንዲያከናውን ይደረጋል ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድርሙስጠፌ ሙሁመድ እና የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በተገኙበት የገንዘብ ርክክብ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች የተለያዩ የልማትና መሰል ጥያቄዎች አንስተዋል።
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ቀደም ሲል በአካባቢው በርካታ ኩባንያዎች ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ የመሥራት ችግር ነበረባቸው ብለዋል፡፡