የማይክሮ አልጌ (ስፓይሩሊና) ምርምርና ማምረቻ ማዕከል ተመረቀ

ሰኔ 13/2016 (አዲስ ዋልታ) በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነው የማይክሮ አልጌ (ስፓይሩሊና) ምርምርና ማምረቻ ማዕከል ተመረቀ።

በባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አማካኝነት ባለፉት 3 ዓመታት የምርምርና የልማት ስራው ሲጠና የቆየው የምርምር ማዕከሉ ግንባታው ተጠናቆ በዛሬው ዕለት በዝዋይ አዳሚ ቱሉ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።

1 ሺሕ 2 መቶ ካሬ ሜትር ላይ ግንባታው ያረፈው የምርምር ማዕከሉ 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የግንባታ ወጪ የተደረገበት ሲሆን በወር ከ30 ኪሎ ግራም በላይ የማይክሮ አልጌ (ስፓይሩሊና) ማምረት እንደሚችል ተነግሯል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ በአልሚ ምግቦቹ ተፈላጊነት ያለውን እና የስነ-ምግብ ይዘቱ ከፍተኛ የሆነውን የስፓይሩሊና ንጹህ ዘር መለየትና ማምረት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተጠቅሷል።

ከኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በአዳሚ ቱሉ ግብርና ምርምር ማዕከል ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ማዕከሉ በቀጣይ የተለያዩ ተቋማትን፣ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ዜጎችን የማስተማር እና የማሰልጠን ስራን ይሰራል ተብሏል።

በግዛቸው ይገረሙ