የምክር ቤቱ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ እየተወያዩ ነው

ተስፋዬ ቤልጂጌ

ታኅሣሥ 26/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ የሥራ አመራሮች በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ይገኛሉ፡፡

ውይይቱ “በዘላቂ ድል ወደ ብልጽግና እንዲሁም የድህረ ጦርነት መዛነፎችና እርምቶች”  በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡

በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ ሀገሪቱ ከተቃጣባት የኅልውና አደጋ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ርብርብ መውጣት መቻሉንና ከፍተኛ አመራሩ በቅርበትና በተደራጀ መልኩ ሲመራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከጦርነቱ በኋላ ሊያገጥሙ የሚችሉ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን በፅናት ታግለን ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ መውሰድ የውይይቱ ዋነኛ ትኩረት ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

ጦርነቱ ያስከተለው ቀውስ እና ውድመት ከባድ ቢሆንም የተገኙትን መልካም እድሎች በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያዊ አርበኝነት፣ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጎልበት፣ የፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ እንደ አዲስ መቀስቀስ፣ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራዎች በአንድነት የቆሙበት እንዲሁም መከላከያ ሰራዊተችንን ለማጠናከር እድል መገኘቱ በጦርነቱ ማግስት የተገኙ መልካም አጋጣሚዎች ስለመሆናቸው የመንግስት ዋና  ተጠሪው በውይይቱ መክፈቻ ገልጸዋል፡፡

በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትና መሰረተ ልማቶችን ማደራጀትና ማቋቋም፣ የተገኘውን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማስጠበቅ እንዲሁም አስተማማኝ ሰላም በማስፈን የኢትዮጵያን ልማትና እድገት ማስቀጠል ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡