“የምዕራብ ዕዝ አሸባሪው ሕወሃትን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ዝግጁ ነው”፦ ሜ/ጀ መሰለ መሠረት

ሐምሌ 23/2013 (ዋልታ) – የምዕራብ ዕዝ የሠራዊት አባላት አሸባሪውን የሕወሃት ቡድን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ በአስተማማኝ የዝግጁነት ቁመና ላይ ይገኛሉ ሲሉ የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜ/ጀ መሰለ መሠረት ተናገሩ።
ጄነራሉ ይህን ያሉት ወደ ምዕራብ ዕዝ የተቀላቀሉትን መሰረታዊ ወታደሮች አቀባበል በተደረገላቸው ጊዜ ነው።
ሜጀር ጀኔራል መሰለ ወደ ምዕራብ ዕዝ የተቀላቀሉትን መሰረታዊ ወታደሮች አቀባበል በተደረገላቸው ጊዜ ህወሀት እንደ እባብ አፈር ልሶ ቢነሳም አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ይዳክራል እንጂ የህልም ቅዠቱ አይሳካለትም ብለዋል።
የዕዙ የሠራዊት አባላት ህግ በማስከበርና የህልውና ዘመቻ ወቅት የአሸባሪውን የህወሓት ቡድን አከርካሪውን በመስበርና የቡድኑን ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ስራ በማዋል ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ የተወጣ ዕዝ ነው ብለዋል።
ዕዙን የተቀላቀሉ የሠራዊት አባላት በበኩላቸው የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው አሸባሪው ህወሓትን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጣቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።