ግንቦት 19/2013 (ዋልታ) – የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ከአለም ባንክ በተገኘ በ150 ሚሊየን ዶላር የማስፍፊያ ስራ እተየሰራ መሆኑ ተገለፀ።
በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀክቲክስ አገልግሎት ድርጅት ካሉት ስምንት ወደቦች አንዱ የሆነው የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል በ2001 ዓ.ም ሲጀምር 20 ሺህ ኮንቴነር በማስተናገድ የጀመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት 133 ሺህ ኮንቴይነር ማስተናገድ እንደምችል ተገልጿል።
80 በመቶው የሀገሪቱ ገቢ እቃዎች የሚያስተናግደው የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል በቀን ሁለት ባቡሮችን በማስተናገድ ላይ ነው። በዚህም በ106 መኪኖች ከ3 እስከ 5 ቀን ድረስ የሚያመላልሱትን እቃዎች በባቡሩ ከ10 እስከ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ማድረስ እንደተቻለ ተጠቁሟል።
የደረቅ ወደብ ተርሚናሉ ከዚህ በፊት 45 ቀናት የነበረው የእቃዎች የወደብ ቆይታ ወደ 7 ቀናት መቀነስ መቻሉም ተነግሯል።
ቅርንጫፉ እየሰጠ ያለውን የደረቅ ወደብና ተርሚናል የሎጀስቲክ አገልግሎት ወደ ሃቭ ሎጅክስቲክስ አገልግሎት ለመቀየር እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል።
ሃቭ ሎጀክስቲክስ አገልግሎት የተሰኘው የገቢ እቃዎችን በመቀበል ብቻ ሳይታጠር የውጭ ንግድን በማሳለጥና የወደብ ቆይታን በማሳጠር የጊዜ፣ የጉልበት እንዲሁም የደህንነት ጉዳዮችን ያሟላና በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት መሥጠት መሆኑ ተነግሯል።
በአሁኑ ሰአት 23 ሺህ የሚደርሱ ኮንቴይነሮችን ለላኪዎች በመስጠት ወደ ውጪ የሚሄዱ እቃዎችን እያሸገ መላክ መጀመሩም ተገልጿል።
በዚህም በተለይ የቡና ወጪ ንግድን ከቅሸባና ስርቆት ማዳን ተችሏል ተብሏል።
የማስፋፊያ ግንባታዎች ከ3 እስከ 25 ቶን የመጫንና የማውረድ አቅም ያላቸውን 49 ክሬን ማሽኖችን በ12 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ወጪ በማስገባት የገቢና ወጪ እቃዎች ኮንቴኖሮች ላይ ፈጣን አገልግሎት መስጠት ያስችላል ነው የተባለው፡፡
ይህም የደረቅ ወደብና ተርሚናል የነበረውን አገልግሎት ወደ 63 በመቶ እንደሚያሳድገው ነው የተገለጸው።
(በምንይሉ ደስይበለው)