የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ተገለጸ

ጥቅምት 11/2015 (ዋልታ) በ150 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው የሞጆ ደረቅ ወደብ የሎጀስቲክ አገልግሎት ማዕከል የማስፋፊያ ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ግንባታው በከፍተኛ ፍጥነት መከናወን እንዳለበት መመሪያ ተሰጥቷል፡፡

ከ400 ሜትሪክ ቶን በላይ አፈር የመቁረጥና ከ30 ሺሕ ቶን በላይ አፈር ሙሌት የተከናወነበት እንዲሁም ለኮንቴነሮች ማራገፊያ የሚሆነውን ወሳኝ የመሬት ንጣፍ ለመስራት የሚያገለግል ኮንክሪት የማምረት ስራ መጀመሩን የፕሮጀክቱ የስራ ሃላፊዎች ገልጸዋል።

ኮንክሪት የማምረት ስራውን የሲሚንቶ እጥረት እየፈተነው እንደሚገኝ ጠቁመው ችግሩን ለመፍታት ግን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አሁን በተያዘው ፍጥነት መቀጠል ከተቻለ በቀጣይ ወራት የፕሮጀክት አፈፃፀሙን ከ50 በመቶ በላይ ማድረስ እንደሚቻል አረጋግጠዋል፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ፤ ፕሮጀክቱ እያደገ ለመጣው የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ የሚኖረውን ከፍተኛ ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት በተጀመረው ፍጥነት ልክ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የፕሮጀክት ማስፋፊያው በታቀደለት ጊዜ ተጠናቆ አገልግሎ መስጠት እንዲችል ለግንባታ ስራው አስፈላጊ የሆኑ በተለይ የሲሚንቶ አቅርቦትን በተመለከተ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በቅርበት በመስራት ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

የሞጆ ደረቅ ወደብ የማስፋፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴን ከማቀላጠፉ ባሻገር ለኢትዮ-ጂቡቲ የኢኮኖሚ ቀጠናዊ ንግድ የላቀ ሚና አለው ተብሏል። የደረቅ ወደቡን ሁለገብ የሎጅስቲክ አገልግሎት ማዕከል በማድረግ ሀገራዊ፣ ቀጠናዊና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችለው መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።