የሠላም ስምምነቱ በሀገራችን የግጭት አፈታት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው- የምክር ቤት አባላት

ጥቅምት 29/2015 (ዋልታ) የሠላም ስምምነቱ በሀገራችን የግጭት አፈታት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተፈረመው የሰላም ስምምነት ሂደት፣ አንድምታ እና በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ የምክር ቤት አባላቱ ውይይት አካሂደዋል፡፡

የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የሰላም ድርድሩ ቡድን አባል ጌድዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት ታጣቂ ኃይሎች መካከል በተደረገው የሰላም ስምምነት ዙሪያ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን በምክር ቤቱ አባላትም ሰፊ ውይይት እና ምክክር ተደርጓል፡፡

የሰላም ስምምነቱ የሀገር ሉአላዊነትና የግዛት አንድነትን ያስጠበቀ፣ ህገ-መንግስታዊነትን የሚያሰፍን፣ በሀገራችን የግጭት አፈታት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እና በአጠቃላይ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያረጋገጠ መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪ መንግስት የሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያ በጥንቃቄ ሊሰራ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

አባላቱ የተጀመረው የሰላም ንግግር በሌሎች አካባቢዎች ያሉ የታጠቁ ኃይሎች ጋርም መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ለዚህም መንግስት እስከ አሁን ለሰላም ያሳየውን ቁርጠኝነት እና በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እያደረገ ያለውን ሁሉ አቀፍ ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በውይይቱ የምክር ቤቱ አባላት እና ሰላም ወዳድ የሆነው መላው ኢትዮጽያዊ ለተግባራዊነቱ ድጋፍ በማድረግ የተጀመረውን የሰላም ስምምነት ማጽናት እንደሚገባ መገለጹን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW