የሩሲያ ኤምባሲ ምንም አይነት የምልመላ ጥያቄዎችን እንደማይቀበል አስታወቀ

ሚያዝያ 12/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ ለ‘ሩሲያ እንዝመት’ የሚሉ ምንም አይነት የምልመላ ጥያቄዎችን እንደማይቀበል ዛሬ በቲውተር ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

እ.ኤ.አ በ1961 በቬና የተፈረመውን ኮንቬንሽን እንደሚያከብርና ምንም ዓይነት የምልመላ ጥያቄዎችን እንደማይቀበልም ነው ያስታወቀው፡፡

የቬናው ኮንቬንሽን የውጭ ሀገር ሰዎችን ለወታደራዊ ሥራ መመልመል ክልክል መሆኑን እንደሚደነግግ ያስታወሰው ኤምባሲው ሩሲያም ድንጋጌዎቹን ታከብራለች ብሏል፡፡

ሩሲያ ያቀደችውን ሁሉ በራሷ ጦር በብቃት እንደምትፈጽም የገለጸው ኤምባሲው በአጋርነት ለቀረቡና ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ክብር እንዳለውም ገልጿል፡፡

ኤምባሲው ኢትዮጵያዊያን በአካል እና በኢ-ሜይል በሚልኳቸው መልዕክቶች እያሳዩ ላሉት አጋርነት አመስግኖ መልዕክቶቹ የሁለቱን ሀገራት ‘የማይሰበር’ ወዳጅነት የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ሩሲያን ለማገድ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መቃወሟ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያያ ሩሲያን ደግፋ ድምጽ መስጠቷም አይዘነጋም፡፡ ለዚህም ኤምባሲው ምስጋና አቅርቧል፡፡

ከሰሞኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በሩሲያ ኤምባሲ በር ላይ ተሰልፈው ታይተዋል፡፡

ይህን ተከትሎ በርካቶች ወጣቶቹ ከሩሲያ ጎን ተሰልፈው ለመዋጋት መሰለፋቸውን ብገልጹም ኤምባሲው ግን ግምቱ ስህተት ነው ብሏል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW