የሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል አባላት የማዕረግ ዕድገት ተሰጣቸው

ጥቅምት 01/2014 (ዋልታ) የቆይታ ጊዜያቸውን ለሸፈኑና የተሻለ የስራ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል አመራርና አባላት የማዕረግ ዕድገት ተሰጠ።

የማዕረግ ዕድገቱ የተሰጣቸው ከባለሌላ ማዕረግተኞች እስከ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች  ናቸው።

ለተሿሚዎች ማዕረግ ያለበሱትና የስራ መመሪያ የሰጡት የመከላከያ የህብረት የሰው ሀብት ዋና መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጄነራል ሀጫሉ ሸለመ፣ በመስዋዕትነትና በጠንካራ የግዳጅ አፈፃፀም ላገኛችሁት የማዕረግ ዕድገት እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

ተሿሚዎችም ባገኙት የማዕረግ ዕድገት ለበለጠ ግዳጅ ዝግጁ በመሆን ያስመዘገቡትን ድል ለማስቀጠል የበለጠ መትጋት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ተሿሚዎች በበኩላቸው፣ የተሰጣቸው የማዕረግ ዕድገት ለሀገራቸው የበለጠ ስራ ለመስራት የሚያነሳሳ በመሆኑ ለቀጣይም የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።