የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይል ለተማሪዎች ግማሽ ሚሊየን ብር የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

መስከረም 12/2015 (ዋልታ) የኢፌዴሪ የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይል ለመካኒሳ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት ተማሪዎች ግማሽ ሚሊየን ብር የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይል የጤና አገልግሎት ኃላፊ ኮሎኔል ሙሉጌታ ተፈራ ድጋፉን ለተማሪዎችና ለወላጆች አስረክበዋል።

በመርኃ ግብሩ ላይ የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይል አመራሮች የመካኒሳ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት መምህራን፣ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው ተገኝተዋል።

ኮሎኔል ሙሉጌታ ተፈራ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የሪፐብሊኩ ዘብ ለሀገር ኅልውና መጠበቅ ከሚያደርገው መስዋዕትነት ባሻገር የህዝብ አጋርና አጋዥ ሠራዊት መሆኑንም በተግባር እያሳየ ነው።

በዚህም ከዚህ ቀደም የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስና ሌሎች የበጎ አድራጎት ተግባራትን ሲያከናውን እንደነበር ጠቅሰዋል።

በ2015 ዓ.ም ለህዝብ የሚያደርገውን በጎ ሥራ በማጠናከር በዛሬው ዕለት ከሠራዊቱ በተሰበሰበ ድጋፍ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ መለገሱን ተናግረዋል።

ይህ መልካም ተግባር የሠራዊቱ የደስታ ምንጭ ነው ያሉት ኮሎኔል ሙሉጌታ በቀጣይም በቻልነው አቅም የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን እናጠናክራለን ብለዋል።

የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይል ፅህፈት ቤት ኃላፊው ኮሎኔል ዓለማየሁ ሙለታ የሪፐብሊክ ጥበቃ ኃይሉ ለህዝብ እንኳን ገንዘቡን ህይወቱን አሳልፎ እየሰጠ በመሆኑ ኩራት ይሰማዋል ብለዋል።

መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎችና ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ በማድረግ የህዝብ ሠራዊትነቱን በተግባር ማሳየቱን ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ሙሴ ዓለማየሁ የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይል ላደረጉት ድጋፍ በተማሪዎችና በትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ሲወሳ የሚኖር በአስፈላጊ ወቅት የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱም ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች ወላጆች በበኩላቸው ሠራዊቱ ለልጆቻችን ላደረገው ድጋፍ እናመሰግናለን ማለታቸውን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።