የሮቤ ከተማ የተቀናጀ የአውቶቡስ መናሃሪያ ተመረቀ


ሐምሌ 05/2013 (ዋልታ) –
ከ290 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት ዘመናዊ የሮቤ ከተማ የተቀናጀ የአውቶቡስ መናሃሪያ ተመረቀ።
መናሃሪያውን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ ጫልቱ ሳኒ እና የትራንፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎንፌ መርቀዋል።
በአንድ ጊዜ ከ600 በላይ አውቶቡሶችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው የተነገረለት ይህ መናሃሪያ፣ በውስጡ የመኪና እጥበትና ጥገና፣ የአሽከርካሪዎች ማደሪያ፣ ምቹ የተሳፋሪዎች መቆያ፣ የንግድ ቤቶች፣ የስበሰባ አዳራሽ እና ሌሎች አስፈላጊ የሚባሉ መሠረተ ልማት የተሟላለት ነው ተብሏል።
መናሃሪያው ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በአሁኑ 11 ተመሳሳይ የከተሞች የተቀናጀ የአውቶቡስ መናሪሃያዎች ጅማ እና ነቀምቴ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ውስጥ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር እየተገነባ እንደሚገኝም በምርቃት ስነሥረዓት ላይ ተገልጿል።
በአሁን ወቅት የኦሮሞ ህዝብ የልማት ጥያቄ እየተመለሰ እንደሚገኝ የገለጹት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ ጫልቱ ሳኒ፣ መንግስት የገባውን ቃል የመፈፀም ኃላፊነት አለበት ብለዋል።
አሁንም ከህብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች እና ወደ ስራ መግባት ያለባቸው ሀብቶች ወደ ልማት የመቀየር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የተለያዩ የልማት ስራዎች አሁንም የክልሉ መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ፣ በቀጣይ የበጀት አመት ከ60 ቢሊየን ብር በላይ ወጭ የሚጠይቁ የልማት ስራዎች እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡
ምክትል ፕሬዝዳንቷ “ለመስራት የግድ ስልጣን ላይ መውጣት አያስፈልግም፤ መስራት የኦሮሞ ህዝብ ባህል ነው፤ ስለዚህ በነዚህ የልማት ስራዎች ላይ መሳተፍ አለባችሁ፤ ያነ የበለፀገች ኦሮሚያን እፈጥራለን” ብለዋል ምርቃት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክታቸው።
የትራንስፖርት ሚኒስትር ድኤታ ካሳሁን ጎንፌ በበኩላቸው፣ መናሃሪያው መገንባት የባሌ ዞን የሮቤ ከተማ የልማት ጥያቄ እንደነበር አስታውሰው፣ ከመናሃሪያው ጋር የሚያያዙ ከተማዋን ከተለያዩ አጎራባች ክልሎች የሚያገናኙ የመንገድ ግንባታዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።
መናሃሪያው የአከባቢውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማሳደግ በኩል ሚናው ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል።
መናሃሪያው ለህብረተሰቡ ዘመናዊ አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ የከተሞችን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ህይወት የሚቀይር የትራፊክ መጨናነቅን የሚያስቀር እና ህገ ወጥነትን በማስቀረት በኩል ሚናው ከፍ ያለ እንደሚሆን የሮቤ ከተማ አአስተዳደር ከንቲባ ደጀነ ደሳለኝ ተናግረዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች እየተሰሩ ባሉ የልማት ስራዎች ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ በከተማቸው በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ስራ አጥ እንደሆኑ አስታውሰዋል፡፡
የልማት ስራዎችን በአግባቡ እየተጠቀሙ ለትውልድ እንዲተላለፍ የማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።
(በሚልኪያስ አዱኛ)