የሰላም ሚኒስቴር መንግሥት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየሠራ መሆኑን ገለጸ

ሰኔ 15/2014 (ዋልታ) መንግሥት በሃይማኖቶች ውስጥ ያለውን የሰላምና የእርቅ እሴቶችን በመጠቀም ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት እንድትሆን በትኩረት እየሠራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።

“ሃይማኖት ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር ዐቀፍ የሰላም ጉባዔ የተካሄደ ሲሆን ሚኒስትሩ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ለሰላም መስፈን ከዘመናዊ የውይይት ሂደቶች በተጨማሪ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ የሰላምና የእርቅ ሥርዓትን መጠቀም አንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ሰላም ከግለሰብ የውስጥ ስሜት ይጀመራል ያሉት ሚኒስትሩ የግለሰቦችን የሰላም እና የመረጋጋት ሁኔታን ለማፅናት የሃይማኖት አባቶች እና መሪዎች ሚናቸው የጎላ መሆኑ እሙን ነው ብለዋል።

ይህንን መልካም የሆነ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት እንዲተገብሩትና ምእመኑን ስለ ሰላምና እርቅ ማስተማር እና ማስገንዘብ የእለት ተእለት ሥራቸው እንዲያደርጉት ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው የክርስትናም ሆነ የእስልምና ሃይማኖቶች ለሰላም መከበርና ለእርቅ ጽኑ አስተምህሮ አሏቸው ብለዋል።

ይሁን እንጂ አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን ከሃይማኖት ጋር ለማስተሳሰር ሲሞከር ማየት እየተለመደ መምጣቱንና ይህንን ሁኔታ ለመቀልበስ የሃይማኖት ተቋማት ተቀራርበው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

የሰላም እጦት ችግር አንገብጋቢ መሆኑን ጉባኤው በጽኑ እንደሚያምን የተገለጹት ጠቅላይ ፀሐፊው ለዚህም አጽንኦት በመስጠት እንደሚሰራ አክለዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ሊጠብቅ እንደሚገባ አንስተው በተለይ ሃይማኖትንና ዘርን መሰረት የሚያደርጉ የጥላቻ አስተምህሮት በሚያስተላልፉ ላይ ተጠያቂነት ያለው ሥራ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ የሃይማኖቶች መከባበር ያለባት ለሌሎች መልካም አርአያ የሆነች ሀገር መሆኗን ያነሱት ተሳታፊዎቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉ ችግሮችን በምክክርና በውይይት መፍታት ያስፈልጋልም ብለዋል።

“ሃይማኖትና ሰላም በኢትዮጵያ እንዲሁም የሃይማኖትና መንግሥት ግንኙነት እና ትብብር” የሚሉ ጥናታዊ ጽሑፎች ለውይይት ቀርቧል።

በሳራ ስዩም