የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ

የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር የበይነ መረብ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ በተባበሩት መንግስታት ዋና መስሪያ ቤት የሰብዓዊ ድጋፍ ዳይሬክተር ሚስስ ሬና ገላኒ እና በተባበሩት መንግስታት አስተባባሪና የሰብዓዊ ድጋፍ የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር ካትሪን ሶዚ ተካፍለዋል።

ሚኒስትሯ በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር ሂደት እንዲሁም ከወታደራዊ ህግ የማስከበር ሂደት ቀድሞ ሰላምን በሰለጠነ መልኩ በውይይት ለማምጣት ስለተሄደው ረጅም እርቀት ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።

በሰላም ማስከበር ሂደቱም ንጹሃን እንዳይጎዱና መሰረተ ልማት እንዳይፈርስ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ የተሞላበት ኦፕሬሽን እንደተካሄደ አስረድተዋል።

ሚስስ ሬና ገላኒ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ መንግስት ንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ የተደረገውን ጥረት አድንቀዋል።

በመጨረሻም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደ ሁልጊዜውም ሰብዓዊና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን ከመንግስት ጋር በገባው የሁለትዮሽ ስምምነት መሰረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።