የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ከጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢማኑዌላ ዴል ሬ ጋር በስልክ ተወያዩ

የሰላም ሚኒስትር  ሙፈሪሃት ካሚል ከጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢማኑዌላ ዴል ሬ ጋር የስልክ ውይይት አካሂደዋል።

ሚኒስትሯ በህወሓት ጁንታ ላይ ሲካሄድ የነበረው ህግ የማስከበር ተግባር መጠናቀቁን እና በሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ስላለው ትብብር ገለፃ አድርገዋል፡፡

የሕግ ማስከበር ሥራው ሲቪሎችንና መሠረተ ልማቶችን ከጉዳት ለመጠበቅ እጅግ በጣም ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ መከናወኑንም ገልፀዋል።

ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በበኩላቸው፣ በሕግ ማስከበር ሂደት ወቅት ሰላማዊ ዜጎችን ለመጠበቅ የተደረገውን ጥረት ያደነቁ ሲሆን የጣሊያን መንግስት በኢጣሊያ የቀይ መስቀል ማህበር አማካይነት በተለይ የህክምና ግብዓቶችን በማቅረብ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ ፍላጎቶችን ለማቅረብ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ አረጋግጠዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀው የወዳጅነት ግንኙነትም የበለጠ እንደሚጠናከር አረጋግጠዋል ፡፡

የሰላም ሚኒስትሯ የጣሊያን መንግስት ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።