የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ልዩ መልዕክተኛ ፓርፌይት ኦናንጋ-አንያንጋ ጋር ተወያዩ፡፡
ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት አብሮነትንና ሀገራዊ መግባባትን ለማዳበር ብሎም ለዘመናት የኖሩ ድንቅ አዋሃጅ እሴቶችን ለማበልጸግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ላይ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ ልዩ መልዕክተኛው አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄዱ ያሉ የማህበረሰብ ተኮር እና የልሂቃን የምክክር መድረኮች እንዲሁም ወጣቱ ከራሱና ከቤተሰቡ አልፎ በማህበረሰብና ሀገር መስተጋብር ማዕቀፍ ውስጥ በመልካምነት፣ በበጎነት፣ አብሮነት እና በፍቅር ማነጽን እሳቤ አድርጎ የተቀረጸውን የብሄራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም አካሄድ ላይ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ልዩ መልዕክተኛው የኢትዮጵያ መንግስት ለዘላቂ ሰላም አስተማማኝ የሆነ አዎንታዊ ለውጥ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
በተጨማሪም የህግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያም ውይይት ያደረጉ ሲሆን በሚያስፈልጉ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትሯ የኢትዮጵያ ወዳጆች አብሮነት ሃገሪቱ ትክክለኛው የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን ከማረጋገጡም በላይ በሀገሪቱ እንዲመጣ ለታለመው አወንታዊ ሰላምና ለውጥ ተጨማሪ ድጋፍ፣ ተስፋና ብርታት ይሆናል ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተለያዩ ዘርፎች እያደረገ ላለው ድጋፍ በኢትዮጵያ ህዝብ፣ መንግስትና በራሳቸው ስም ምስጋና ማቅረባቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡