ሐምሌ 11/2013 (ዋልታ) – የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በጀርመን እና እንግሊዝ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አደረጉ፡፡
ሚኒስትሯ በጉብኝታቸው ለጀርመን የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ሚጉዌል በርገር እንዲሁም ለእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ጄምስ ዱድሪጅ እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የአንድ ወገን የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ለማድረግ ሲወስን በዋነኝነት የትግራይን ህዝብ ከተጨማሪ ሰብዓዊ ቀውስ ለመታደግና የእርሻ ወቅት አልፎ በመጭዎቹ ዓመታት የምግብ እጥረት ቀውስ እንዳይገጥም ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ለህዝቡ ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ምግብ እንዲሁም ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን እና ነዳጅ በመጋዘኖች ክምችት መቀመጡን ገልፀዋል።
በተጨማሪም በተመረጡ 6 የሰብዓዊ እርዳታ አጋሮች በኩል የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ እስከ አሁንም የቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም የአለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የህወሃትን አጥፊ አቋም ተረድቶ በግልጽ ማውገዝ እንደሚገባው በአጽንኦት ተናግረዋል።
እስከ አሁን ለተደረገው ሰብዓዊ ድጋፍም አመስግነው ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከሰላም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመላክቷል።