የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል 229 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የሕክምና ቁሳቁስ መሰራጨታቸው ተገለጸ

ታኅሣሥ 7/2015 (ዋልታ) የሠላም ሥምምነቱን ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል 229 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የህክምና ቁሳቁስ መሰራጨታቸውን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ገለጸ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ  እንዳሉት የሰላም ሥምምነቱን ተከትሎ በሦስት አቅጣጫዎች መድኃኒቶች ወደ ትግራይ ክልል እየተሰራጩ ነው።

በዚህም በመጀመሪያው ዙር 229 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የህክምና ግብዓቶች ወደ ትግራይ ክልል መላካቸውን ጠቁመው በመቀሌ እንዲሁም በሽሬ የሚገኙ የአገልግሎቱ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በከፊል ሥራ መጀመራቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የመድኃኒቶቹ ዓይነትም የጤና ፕሮግራም መድኃኒቶች (የኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ የወባ እንዲሁም የእናቶችና ህጻናት መድኃኒቶች) እንደሆኑ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለመደበኛ፣ ለሕይወት አድን የሚውሉ መሰረታዊ መድኃኒቶች፣ ለህክምና አገልግሎትና ለላቦራቶሪ ግብዓት የሚውሉ ኬሚካሎች መሰራጨታቸውንም አብራርተዋል።

እንደ ስኳርና ደም ግፊት የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለማከም የሚያገለግሉ መድኃኒቶች መካተታቸውን ገልፀው ሁለተኛ ዙር የመድኃኒት ሥርጭትም በቀጣዮቹ ቀናት እንደሚጀመር ጠቁመዋል።