የሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ተባለ

ጥቅምት 28/2015 (ዋልታ) በመንግስትና ህወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ተፈፃሚ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የፓለቲካል ሳይንስ ምሁርና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት ፕሮግራም ዳይሬክተር ተናገሩ፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት በፌደራል መንግስቱና ህወሃት መካከል በተደረገ ጦርነት በርካታ ዜጎች ህወታቸውን ሲያጡ በርካቶች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡

በጦርነቱ የተነሳም በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከመድረሱም ባሻገር አገር ሰላም እንዳትሆን የሚፈልጉ ሀይሎች ጦርነቱ እንዲባባስ የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት አፍሪካዊያን ችግሮች በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት መፈታት አለባቸው የሚል ፅኑ አቋም በመያዝ ለሰላም ያለውን ዝግጁነት በተደጋጋሚ አሳይቷል፡፡

በዚህ መሰረትም በህወሀት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሰላም ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ተፈርሟል፡፡

ዋልታ ያነጋገራቸው የፓለቲካል ሳይንስ ምሁርና  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት ፕሮግራም ዳይሬክተር የቻለ ደጉ (ፒኤችዲ) በፌደራል መንግስቱ እና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ እንድትታመስና ሰላም እንዳትሆን ለሚፈልጉ አካላት መልስ የሰጠ ከመሆኑም ባሻገር ሰላም ለሁሉም ነገር አማራጭ መሆኑን ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

በአፍሪካ አገራት ግጭቶች ሲነሱ ምዕራባዊያን አገራት አፍሪካ ላይ ጫና ለማሳደር በተደጋጋሚ ጥረት እንደሚያደርጉ የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ በፌደራል መንግስትና በህወሃት መካከል የተፈጠረው ችግር በአፍሪካ ህብረት እንዲፈታ ከመጀመሪያው ጀምሮ ፅኑ አቋም እንደነበራት ገልፀዋል፡፡

በፌደራል መንግስትና በህወሃት መካከል  በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት አፍሪካዊ ችግሮች በአፍሪካዊያንና በአፍሪካ ህብረት መፍታት እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የተናገሩት ምሁሩ ለስምምነቱ ተፈፃሚነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተለይም በህዝቦች መካከል መቀራረብ እንዲፈጠር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበትም ነው የገለፁት፡፡

በፌደራል መንግስትና በህወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ተፈፃሚነቱ የተሳካ እንዲሆን በትብብር መስራት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

በሱራፌል መንግስቴ