የሰላም ስምምነቱ እንዲሳካ ያደረጉ ሁሉም ተሳታፊዎች ምስጋና ይገባቸዋል- ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ጥቅምት 27/2015 (ዋልታ) ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመንግስትና በህወሃት መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት በስኬት እንዲጠናቀቅ ውሳኔ ላሳለፉት የሁለቱም ወገን ተሳታፊዎች ምስጋና አቀረቡ።
አዲስ አበባ ከተማ በአርጀንቲና እና ብራዚል ላገኘችው ዓለም አቀፍ ሽልማት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በሚሊኒየም አዳራሽ በተከናወነ የእውቅና መርሐ-ግብር ተገኝተው ፕሬዝድንቷ ባስተላለፉት መልዕክት “በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ሁላችንንም አረጋግቷል፤ እፎይ እንድንልም አድርጎናል” ብለዋል።
የዚህ ዓይነት ስምምነት ላይ መድረስ ድፍረትና ታሪክን ይጠይቃል ያሉት ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ የሁለቱም ወገን ተደራዳሪዎች በደረሱት የፖለቲካ ውሳኔ ላስገኙት ውጤት ምስጋና አቅርበዋል።
በእርስ በእርስ ጦርነት አሸናፊ የለም ያሉት ፕሬዚደንቷ በተደረሰው ስምምነት አሸናፊዋም ኢትዮጵያ ነች ብለዋል።
“የተሰበረውን መጠገን፣ የተጎዳውን ማጽናናትም የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት ነው” ብለዋል።