የሰሜን ኮሪያ አዲስ ረጅም-ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ

መስከረም 03/2014 (ዋልታ) ሰሜን ኮሪያ አብዛኛውን የጃፓን ክፍል ሊመታ የሚችል አዲስ የረጅም ርቀት ሚሳኤል ሙከራ ማካሄዷን የአገሪቱ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

ቅዳሜና እሁድ በተካሄዱት ሙከራዎች ሚሳኤሎቹ እስከ 1,500 ኪ.ሜ ርቀው ስለመጓዛቸው ኮሪያን ሴትንራል የዜና ማዕከል ዘግቧል።

ሙከራው አገሪቱ ካለችበት የምግብ እጥረት ብሎም የኢኮኖሚ ቀውሶች ችግር ባሻገር አሁንም የጦር መሳሪያዎችን የማምረት አቅም እንዳላት ያመላከተ ነው ተብሏል።

ይህ የረጅም ርቀት ሚሳኤል ሙከራ “በተለይም የአገራችንን ደህንነት ለማስጠበቅ በምናደርገው ጥረት ውስጥ ስትራቴጂካዊ የሆነ ጥቃትን የማስቆም አቅም የሚያስገኝ ብሎም የጠላት ኃይሎችን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለማስቆም የሚያስችል ይሆናል” ነውም የተባለው።

የጃፓን ካቢኔ ዋና ፀሐፊ ካትሱቡ ካቶ በበኩላቸው፣ ጉዳዩ መንግሥታቸውን ያሳሰበ መሆኑን እና መፍትሄውን በተመለከተም ከአሜሪካ እና ከደቡብ ኮሪያ ጋር እየሰራ መሆኑን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የአሜሪካ የጦር ኃይል ሙከራው ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ መርኃግብሯን ለማሳደግ ያላትን እቅድ ብሎም ለጎረቤቶቿም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የደቀነችውን ስጋት ያሳያል ሲል ድርጊቱን አውግዟል።

አክሎም አሜሪካ ወዳጅ አገሮቿ የሆኑትን ደቡብ ኮሪያን እና ጃፓንን ለመከላከል የያዘችው ቁርጠኛ አቋም አሁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጿን ቢቢሲ ዘግቧል።