ሰኔ 24/2013 (ዋልታ) – የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ብሔራዊ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ግንባታ በዛሬው ዕለት አስጀምሯል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በአሁኑ ወቅት የሥራ ፈላጊ መረጃዎች ቀጥርና የገበያ መረጃው ተመጣጣኝ ያልሆነ መሆኑን አንስተው፣ ይህንን ችግር ለመፍታት ዘመናዊ የሥራ መረጃ ስርዓት ለማዘመን በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም የመረጃ ሥርዓቱ የልማት ፖሊሲዎችን ወደ ተግባር መቀየርና ወጣቱ ወደ ተለያየ የሥራ ዘርፍ እንዲሰማራ ለማድረግ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።
በመርኃግብሩ ላይ በኢትዮጵያ ዘመኑን በሚመጥኑ መልኩ መረጃዎችን ማደራጀት የሚል ዓላማ ያለው መሆኑም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የነበራት የሰራተኞች የመረጃ አያያዝ፣ ቅርፅ አልባ፣ የተበጣጠሰና ተዓማኒነት የጎደለው እንደነበር የተገለፀ ሲሆን፣ ይህ የተዳከመ የሰራተኞች መረጃ አያያዝ ሰራተኛን ከአሰሪው ማገናኘት ያልቻለ መሆኑ ተጠቁሟል።
በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው የብሔራዊ የስራ መረጃ ማዕከል ይህንን ችግር ለመፍታት የሚያስችልና ባለድርሻ አካላትን ማስተሳሰር የሚችል ሥርዓት ነውም ተብሏል።
የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመድ መሀመድ አስተማማኝና የተጠቃሚውን ፍላጎት ማሟላት የሚችል መረጃን መሰብሰብ የሚችሉ ባለድርሻ አካላት በርካታ መሆናቸውን ገልፀው፣ በትብብር ሥርዓቱን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
(በዙፋን አምባቸው)