የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር ዓመታዊ በዓል በእንጅባራ እየተከበረ ነው

 

በአማራ ክልል አዊ ዞን 81ኛው የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር ዓመታዊ በዓል ዛሬ በእንጅባራ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ዘውዲቱ ወርቁ እንደገለጹት፤ በዓሉ ትውፊቱን ጠበቆ እንዲከበር በማድረግ ለቱሪዝም አገልግሎት እንዲውል ለዓለም ማህበረተሰብ ለማስተዋወቅ እየተሰራ ነው።

በዓሉ በፈረስ ጉግስ፣ በስርጥና በሌሎችም ውድድሮች እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ካለፉት አራት አመት ወዲህ በዓሉን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን አመልከተዋል።
በዓሉ ቀደም ሲል በጣሊያን ወረራ ወቅት ፈረስና ፈረሰኞች ያበረከቱትን አስተዋጻ ለማስታወስ ይከበር እንደነበር አስታውሰዋል።

በተለይም ማህበሩ 78ኛ ዓመቱን ካከበረበት ካለፉት አራት አመት ጀምሮ አካባቢውን የቱሪዝም መዳረሻ ለማደረገ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በእንጅባራ ከተማ እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ እየተከበረ ባለው የማህበሩ በዓል ላይ ከፌዴራልና ክልል የተውጣጡ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የስራ ሀላፊዎች፣ ህብረተሰቡና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።
የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር ከ53ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ታውቋል። (ምንጭ፡-ኢዜአ)