የሰብኣዊ ድጋፍ የጫኑ 30 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ለመጓዝ ዝግጁ መሆናቸው ተጠቆመ

ሚያዝያ 12/2014 (ዋልታ) የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሰብኣዊ ድጋፍ የጫኑ 30 ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ለመጓዝ ዝግጁ መሆናቸውን አስታወቀ።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ክሌር ኔቪል ለኢዜአ እንደገለጹት ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚያስፈልጉ አቅርቦቶችና አልሚ ምግቦችን የያዙ 30 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ለመጓዝ ዝግጁ ሆነዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ መንግሥትን የሰብኣዊ ተኩስ አቁም ውሳኔ በበጎ ጎኑ ያየዋል ያሉት ኃላፊዋ ተቋሙና አጋሮቹ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚያስፈልገውን ሰብአዊ ድጋፍ የማድረስ አቅም አላቸው ብለዋል።

በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ፣ አፋርና አማራ ክልሎች የምግብ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ውስጥ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚሁ መሰረት ተቋሙ በትግራይ ክልል 2 ነጥብ 13 ሚሊየን፣ በአማራ ክልል 650 ሺሕ እና በአፋር ክልል 630 ሺሕ ሰዎችን ለመደገፍ ማቀዱን ኃላፊዋ አብራርተዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከእ.አ.አ 2021 መግቢያ አንስቶ በአፋር፣ ትግራይና አማራ ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ወገኖች የሕይወት አድን የምግብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።