መስከረም 5/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ታላቁን የጀርመን-አፍሪካ 2021 ሽልማት መሸለማቸው ተገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ የጀርመን ኢምባሲ በቲውተር ገጹ እንዳስታወቀው የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን ዶክተር ዳንኤል ለሰብዓዊ መብት ባላቸው ቁርጠኝነት ሽልማቱን ማግኘታቸውን ገልጿል፡፡
ሽልማቱ ስም ካላቸው የጀርመን ሽልማቶች ቀዳሚው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዶ/ር ዳንኤልን የሽልማቱ አሸናፊ አድርጎ መምረጡን ፋውንዴሽኑ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
ዶ/ር ዳንኤል ለሽልማቱ ታጭተው ከነበሩ 30 ሰዎች መካከል ቀዳሚ ሆነው ከፍተኛውን ሽልማት ያገኙ ሲሆን፣ 24 አባላት ያሉት ገለልተኛው የዳኞች ጉባዔም ዶ/ር ዳንኤልን አሸናፊ አድርጎ በሙሉ ድምጽ መምረጡ ታውቋል፡፡
ኮሚሽነር ዳንኤል በመጪው ህዳር ወር በሚዘጋጀው ይፋዊ ስነሥርዓት ሽልማቱን እንደሚቀበሉም ተገልጿል፡፡
ሶማሊያዊቷ የሰላም አቀንቃኝ ኢልዋድ ኢልማን የባለፈው ዓመት የሽልማቱ አሸናፊ እንደነበረች መረጃዎች ያመለክታል፡፡