የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ የችግሩን ውስብስብነት ሊመጥን የሚችል ፈጣን ምላሽ መስጠት ያሰፈልጋል ተባለ

መጋቢት 27/2014 (ዋልታ) በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች በፌዴራል አስፈፃሚ አካላት የተጀመረው የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ የችግሩን ውስብስብነት ሊመጥን የሚችል የላቀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።
የብሔራዊ አደጋ መከላከል ኮሚቴ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች በሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ አጠቃላይ እንቅስቃሴውን ገምግሟል።
የብሔራዊ አደጋ መከላከል ኮሚቴ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ በአሁን ጊዜ መንግሥት በጦርነት እና በድርቅ የተጎዱ አካቢዎች የሚኖሩ ወገኖችን በሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርገው ሁሉዐቀፍ እንቅስቃሴ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
ችግሩ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የተጀመረው እንቅስቃሴ አበረታች ቢሆንም ከችግሩ ውስብስብነት አኳያ የሚመጥን ፈጣን ምላሽና ቅንጅታዊ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከጠላት ቁጥጥር ነፃ የወጡ አንዳንድ ቦታዎችን በሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስልት ነድፎ መንቀሳቀስ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።
የፌዴራል አስፈፃሚ አካላት እንደሃገር የገጠመንን ሰፊ እና ውስብስብ ፈተና በአጭር ጊዜ መፍትሄ ለማበጀት ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶ በጋራ መረባረብ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
በሀገሪቱ የተፈጥሮ እና የሰው ሰራሽ አደጋዎች ተደራርበው መከሰታቸው እርምጃችንን ፈታኝ ቢያደርገውም፤ በተግባር ልንሻገር የሚያስችል የተናበበ ዕቅድ፣ ግልፅ አሰራርና ውጤታማ የሃብት አጠቃቀም ስልት ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።
ከሳዑዲ ተመላሽ ወገኖችን ተቀብሎ በማስተናገድ ሂደት የሚገጥሙ ችግሮችን በፍጥነት እየፈቱ በአግባቡ ከቤተሰቦቻቸው የሚቀላቀሉበትን መንገድ የጋራ አፅንዖት እና ምላሽ እንዲሰጠው ጥሪ ማቅረባቸውን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡