ሐምሌ 03/2013 (ዋልታ) – የሰብዓዊ ድጋፍ የጫኑ 40 ያህል ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እየሄዱ ነው።
መንግስት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል።
የዚህ አንዱ ማሳያ የሆነው ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን የማድረግ ጥረት ተጀምሯል።
በዚህም ቁጥራቸው 40 ያህል የሆኑ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከባድ ተሽከርካሪዎች ከአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ ተነስተው ወደትግራይ በማቅናት ላይ ይገኛሉ።
መንግስት በቅርቡ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለትግራይ ህዝብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ መንግስት ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በክልሉ ከተደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ ውስጥ 70 በመቶ በመንግስት ሲሸፈን 30 በመቶው ደግሞ በእርዳታ ሰጪ አጋሮች መሸፈኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ያልተገደብ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ እንዲችል ልዩ የበረራ ፈቃድ መስጠቱ እንደሰጠም ይታወቃል።